0
Posted March 23, 2014 in Amharic news
 
 

“ውሃ፣ መብራት፣ ኔትዎርክ የለም ፤ ኑሮ ከበደን” ሰሚ ጆሮ ያጣ የሕዝብ እሮሮ


“ውሃ የለም፤ መብራት፤ ኔትዎርክ የለም፤ መብት የለም፤ ፍትህ የለም፤ ኑሮ ከበደን” እያሉ ስለኑሮዓቸው የተሰማቸውን በሀቅ የተናገሩ ልጃገረዶች በጋጠወጥ የህወሓት ካድሬዎችና ታጣቂዎች እጅ መከራና ስቃይ እየደረሰባቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነዚህ ለጋ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ በዝምታ ያልፋል ተብሎ አይታመንም።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮን ጨምሮ በወያኔና የጥቅም ተጋሪዎቹ ሥር የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን በየዕለቱ ያለማቋረጥ ከሚዘገቡት የልማትና የዕድገት ዘገባዎች ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዘው በአገራችን ውስጥ እየተሠሩ ስላሉ ትላልቅ የሃይድሮ ኤለክትሪክ ማመንጫ ግንባታዎች፤ በየከተማው ስለተዘረጉ የውሃ መስመሮች፤ የስልክ አገልግሎት ለማዳረስ ስለተወሰዱ እርምጃዎች፤ ስለ ረጃጅም የባቡር መስመሮች ግንባታ እና ስለ አገር አቋራጭ የመንገድ ሥራዎች የሚቀርቡ የተጋነኑ ዘገባዎች ናቸው።

እነዚህ የልማት አውታሮች ግንባታ በአብዛኛው የሚካሄዱት ከምዕራባዊያን መንግሥታት በሚሰጡ የገንዘብ እርዳታና ዕዳው ለልጅ ልጆቻችን በሚተርፍ አለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶች ወለድ እያስከፈሉ በሚሰጡት የረጅም ጊዜ ክፍያ ብድር እንደሆነ ግልጽ ነው።

ወያኔ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 23 አመታት በድህነት ቅነሳና የልማት ማስፋፊያ ስም ከአለም አቀፍ ኅብረተሰብ የተቀበለው የገንዘብ መጠን ሲሰላ ኢትዮጵያ አገራችን እንደ አገር ከተመሰረተችበት ዘመን ጀምሮ በብድርም ሆነ በእርዳታ ስም ይህንን ያህል መጠን ገንዘብ አግኝታ እንደማታውቅ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ ። በዚህም መሠረት ገንዘቡ በአግባብ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አገራችን የትና የት በደርሰች ነበር እያሉ የሚቆጩ የአገሪቱ ልሂቃንና ቅን አሳቢ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም ።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ከ3 አመት ገደማ በፊት ይፋ ባደረገው አንድ መረጃ ወያኔ ሥልጣን በተቆጣጠረባቸው የመጀመሪያዎቹ 9 አመታት ብቻ ከ11.5 (አሥራ አንድ ነጥብ አምስት ) ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በህገወጥ መንገድ ከአገር አሽሽቶ በምዕራባዊያን አገሮች ባንኮች ደብቆአል ። ይህ ከደሃው ጉሮሮ ተቀምቶ በባለሥልጣናቱ የተዘረፈና በህገወጥ መንገድ ከአገር የሸሸው 11.5 ቢሊዮን ዶላር በትክክል ልማት ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ወያኔዎች “ባለ ራዕዩ መሪያቸን” በሚሉት ዘረኛው መለስ ዜናዊ ሥም ለመሰየም ደፋ ቀና የሚሉትን ጅምር “የህዳሴ ግድብ” አይነቱን ሁለት ግዙፍ ግድቦችን በመገንባት የአገሪቷን ገጽታ አበላሽቶ የኖረውን ረሃብ ከምንጩ ማጥፋት ይቻል ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአገሪቱ የሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ “ውሃ የለም፣ መብራት የለም፣ ኔትዎርክ የለም። የሚላስ የሚቀመስ ነገር ማግኘት ተስኖናል፤ ኑሮ ከአቅማችን በላይ ሆኖአል። ትዳር መስርተንና ልጆች ወልደን እያሳደግንበት ካለው የደሃ ጎጆዎቻችን በቀበሌ ካድሬዎች ትዕዛዝ ቤቶቻችን በዶዘር ላያችን ላይ እንዲፈርስ ተደርጎ ሜዳ ላይ ተበትነናል። ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጊዜ ጀምሮ እንገለገልበት ከነበረው የእርሻ ማሳችንና የግጦሽ መሬታችን ተነቅለን ዓይኖቻችን እያዩ ከህንድ፣ ከቻይናና ከአረብ አገር የመጡ ከበርቴዎች መሬታችንን ተቀራምተውታል። አቤት የምንልበት አጣን። ኑሮ መሮናል!!!” የሚሉ እሮሮዎች የወያኔ አፈና የፈጠረውን የፍርሃት ዝምታን ሰብሮ ከአጥናፍ አጥናፍ እየተሰማ ነው።

ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየከረረ የመጣውን የሕዝብ እሮሮ ለማዳመጥ ጆሮ ያልፈጠረበት የዘረኛው ህወሓት አገዛዝ ግን “ነጋ ጠባ የሚደሰኮረው ልማት ምድር ላይ ጠብ አላለልንም፤ መሠረታዊ ችግሮቻችን ከመፍታት ይልቅ እያባባሰ ያለው ምን የሚሉት ልማት ነው?” ብሎ የጠየቀውን ሁሉ “ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ሰላም፣ ሽብርተኞ” የሚል ስም እየለጠፈበት ማሰር ማዋከብና ማሳደድ የዘወትር ተግባሩ አድርጎታል።

በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ አለም አቀፍ የሴቶች በዓል ሲከበር ይኸው የሕዝብን ብሶት ባስተጋቡት ወጣት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ የዚህ የወያኔ አፈና እርምጃ ማሳያ ነው። “ብሶት የፈጠረኝ ነኝ” የሚለው ህወሓት፤ ብሶት እሱን ብቻ ፈጥሮ የመከነ ይመስለዋል።

ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ እያካሄድኩ ነው በሚላቸው ትላልቅና ትናንሽ ግንባታዎች መጠነ ሰፊ ብዝበዛና ዘረፋ እያካሄደ መሆኑን የሚያጋልጡ በቂ መረጃዎች አሉት። የወያኔ ልማትና እድገት ማሳያ ተደርጎ ከሚጠቀሱ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ግንባታ አንስቶ በመላው አገሪቱ ለሚሠሩ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በሙሉ የሚያስፈልጉ የግንባታ ዕቃዎች ስምንቶ፤ አሸዋና ብረታ ብረት የመሳሰሉትን የሚያቀርቡት በባለሥልጣናቱ ንብረትነት የሚታወቁና በቤተሰቦቻቸው ወይም የቅርብ ዘመዶቻቸው ስም የሚተዳደሩ የግል ድርጅቶች ናቸው። የግንባታዎቹን ሥራ ደግሞ የሚያካሂዱት በወያኔ ንብረትነት የሚታወቁ የኢፈርት ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ናቸው። በዚህ አይነት ኮንትራት ሰጪ፤ ኮንትራት ተቀባይና ዕቃ አቅራቢ በመሆን በሚበዘበዘውና በሚዘረፈው የሕዝብ ሃብት የወያኔ ሹማምንትና ግብረ አበሮቹ እስከ ልጅ ልጆቻቸው በልተው የማይጨርሱትን ሃብት አግበስብሰዋል።

ይህ አልበቃ ብሎአቸውም አይናቸው ያረፈባቸው ቁልፍ የከተማ ቦታዎች ላይ የሰፈረውን ደሃ ሕዝብ በማፈናቀልና ጎዳና ላይ በመበተን ረጃጅም ፎቆችን እየሰሩ በማከራየት ሥራ ላይ ተጠምደዋል። ከአመታት በፊት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች የያዙትን ቦታ ለማስለቀቅ ሆን ተብሎ ንብረታቸው በእሳት እንዲወድም ተደርጎአል። በሕይወት ዘመናቸው ያፈሯት ሃብት በእሳት እንዲጋይባቸው የተደረጉ ዜጎች አቤት የሚሉበት ስላልነበራቸው ሥራ አጥና የጎዳና ተዳዳሪ ለመሆን ተገደዋል። ባለፈው ሁለት ሳምንት ተመሳሳይ እርምጃ ሀረር ከተማ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ በተሰማሩት ወገኖቻችን ላይ ደርሶ እንባ ሲራጩ ተመልክተናል።

ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በልማት ስም በወገኖቻችን ላይ የሚፈጽመውን የማፈናቀል ዘመቻ ማስቆም የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው ብሎ ያምናል። ሕዝባችን በጨለማ እየተሰቃዬ ከደጃችን የሚመረት የመብራት ኃይል ወደ ጎረቤት አገር እየተላከ ለማይጠረቃው የወያኔ ሃብት የማጋበስ ጥማት ማርኪያ መሆን ማስቆም የምንችለው እኛው ብቻ ነን። ወገኖቻችን በረሃብ አለንጋ እየረገፉና ነፍሰ አድን የምግብ እርዳታ ከፈረንጅ በምጽዋት እየተቸረን በምድራችን የሚመረት እህል ባህር አቋርጦ ለባለጸጋ አገሮች ገቢያ ሲውል አይተን እንዳላየን ማለፉን ማስቆም የኛ ተግባር ነው። ዕዳው ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ የብድር ገንዘብ በየአመቱ አገር ውስጥ በገፍ እየገባ እናቶችና ህፃናት በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት መሰቃየታቸውን ማስቆም የምንችለው እኛው ነን። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት በቂ የትምህርት እድልና የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ገንዘብ በሙስናና በሌብነት በተጨማለቁ የአገዛዙ ሹመኞች መዘረፉን ማስቆም ያለብን እኛው ነን።

“ውሃ የለም መብራት የለም ኑሮ ከአቅማችን በላይ ሆኖ መኖር አቅቶናል” የሚለውን የወገን እሮሮ ያሰሙ ልጃገረዶችን ድምጽ መስማት ግዴታችን ነው። የእነዚህ ወጣቶች አርዓያነትን በመቀበል ዛሬውኑ የትግሉን ጎራ በመቀላቀል እብሪተኛውንና ዘረኛውን የወያኔ አገዛዝ ፍጻሜ በማፋጠን ነፃነታችንን እንድንጎናጽፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!