0
Posted December 16, 2013 in Amharic news
 
 

ነጋሪቱም ተጎስሟል፤ፋኖም ተሠማርቷል !!!


ዛሬ ኢትዮጵያዊያን እያዩ ያሉት ውርደት ቃል የሚገልፀው አልሆነም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ዛሬ እየደረሰ ያለ ዓይነት ውርደት ደርሶባት እንደሆነ በታሪክ የተመዘገበ ነገርም ተፈልጎ አልተገኘም። ይሄ ለኢትዮጵያዊያን የጨለማ ዘመን ነው። በኢትዮጵያ እንዲህ ስደትና እንግልት፤ ሃዘንና ዋይታ የበዛበት ዘመን ታይቶ አይታወቅም።

በዚህ ግዜ በኢትዮጵያችን መንግስት ነኝ እያለ ራሱን የሚጠራ ቡድን አለ።ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ የገባችበት የውርደት አዘቅት ከባድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በህወሃቶች አዝማችነት ተስምቶ የማይታወቅ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ግፍ በዜጎች ላይ ይፈፀማል። የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ይዘው ግብረ ሶዶም እንዲፈፀምባቸው ያደርጋሉ፤ ሴቶች ልጆችን በጋራ ሁነው ይደፍራሉ፤ በተቀደሱ ስፍራዎች ገብተው ቅዱሱን ስፍራ ያረክሳሉ፤ ዜጎችን ከእርሻ ማሳቸው አፈናቅለው በገዛ አገራቸው መፃተኛ ያደርጓቸዋል። በአጠቃላይ ዜጎች በአገራቸው ተስፋ አጥተው ሃዘንተኛ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ተስፋ የቆረጡ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከምኖር ሂጄ ብሞት ይሻለኛል ብለው እግራቸው በመራቸው መንገድ ይሰደዳሉ። በእንዲህ ሁኔታ ከኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ250ሺህ በላይ ወጣቶች ይሰደዳሉ።ገሚሱ በየበርሃው በውሃ ጥማት ወድቆ ይቀራል፤ ገሚሱም የባህር አዞ ቀለብ ሁኖ ዱካው ይጠፋል። ከሞት ተርፈው በየአርብ አገራቱ የደረሱ ዜጎች በሰው ልጆች ላይ ሊደርስ የማይገባ ወንጀል ይፈፀምባቸዋል።ባንዲራቸውን በአንገታቸው እንደጠመጠሙ ሬሳቸው ሜዳ ላይ ተጥሎ የአርብ መሳቂያ መሳለቂያ ይሆናሉ። በዚህ ሰሞን በሳውዲ ዓረቢያ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ብሄራዊ ውርደት ሁኗል።

ይሄ በእንዲህ እንዳለ “መንግስት ነኝ “ እያለ ራሱን የሚጠራው ህወሃት በዜጎቹ ሲቃና መከራ እየቀለደ ይገኛል።አንድ ግዜ ዜጎቼን እያወጣሁ ነው ይላል፤ ሌላ ግዜ ደግሞ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ስለሆኑ አላውቃቸውም ይላል። ህወሃቶች በዚህ ብቻ አላበቁም በኢትዮጵያዊያኑ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ለማስቆም አዲስ አበባ በሚገኘው በሳውዲ እምባሲ ፊት ለፊት ሠላማዊ ሠልፍ እንዳይደረግ መከልከል ብቻ ሳይሆን ለሠላማዊ ሰልፍ የወጡ ዜጎችን የቻሉትን ያክል ወደ እስር ቤት አግዘዋል፤ ያገኙትን ሁሉ በቆመጥ እንዲደበደቡ አድርገዋል። የአካል ጉዳትም አድርሰዋል። ይሄን ሁሉ ግፍ የሚታደግ፤የህዝቡንም ሮሮ የሚሳማ መንግስታዊ አካል አልተገኘም። ዓለምም ፊቷን ያዞረችብን የሚመስል ሁኔታ ታይቷል።

ኢትዮጵያዊያን ቀና ብለን በኩራት በአርብ አገራት ጎዳናዎች ላይ የምንመላለስ ዜግች ነበርን። ስማችን ያማረ፤ ማንነታችን የተከበርን ዜጎች ነበርን። አረብ የሚያከብረን እንጂ እንዲህ የሚንቀንና የሚያዋርደን ዜጎች አልነበርንም። በዘመነ ህወሃት ግን ያ ሁሉ ክብራችን ተዋርዶ ዜጎቻችን እንደ ሌጦና ቆዳ በገንዘብ የሚሸጡ ሆኑ። በኢትዮጵያችን ላይ የነበሩ የቀድሞው ገዥዎች ምንም እንኳ ጨቋኞች ቢሆኑም ዜጎቻቸው በሌላ በማንም እጅ እንዲገላቱና እንዲዋረዱ የሚፈቅዱ አልነበሩም።በአንድ ወቅት አፄ ኃ/ስላሴን” ሠራተኛ ይላኩልኝ” ብለው የሳውዲው ንጉስ ሲጠይቋቸው “ለመሆኑ ምንድ ነው የምትፈልጉት መሃንዲስ ነው ወይስ ሃኪም “ብለው ይጠይቋቸዋል። አይ “እኛ የምንፈልገው በቤት ሠራተኛነት የሚያገለግሉንን ነው” ይላሉ አረቦቹ።አይ “እኛ ለቤት ሠራተኛ የሚሆን ዜጋ የለንም” ብለው መለስውላቸዋል።ለራሱም ሆነ ለወገኑ ክብር ያለው መሪ መልሱ እንዲህ እንጂ ሳውዲ ድረስ ሂዶ ዜጎቹን ለባርነት ለመሸጥ ሲዋዋል አይገኝም።

ደሳለኝ ኃ/ማሪያም ከስድስት ወር በፊት ሳውዲ ድረስ ገስግሶ ሂዶ የቤት ሠራተኞችን ለአረቦቹ ለመላክ ተዋውሎ መመለሱ የሚታወስ ነው። ይሄን ውል ሲዋዋል ግን ስለ ክፍያ፤ ስለ ዕረፍት ግዜ፤ በህመም ግዜ ምን ይሆናል የሚሉ መሠረታዊ ቁም ነገሮች በውሉ ውስጥ አልተካተቱም። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የኢንዶኔዥያ እና የፊሊፕልንስ መንግስታት ግን ምንም እንኳ ድሃ ብንሆንም ዜጎቻችንን የምንሰደው የታወቀ የክፍያ መጠን፤ የእረፍት ግዜ፤ የህመም ፈቃድ እነዚህንና ሌሎችን መሠረዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የተሟላ የህግ ድንጋጌ ሲኖራችሁ ነው። ይህን ህግ እስከምታበጁ ዜጎቻችን የእናንተ መጫወቻ እንዲሆኑ አንልክም ብለው እምቢ ማለታቸው ይታወቃል። ህወሃት መራሹ መንግስት ግን ስለውጪ አገር አኗኗር ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸውን ወጣት ልጆችን ያለ ምንም ህግ ከለላ አሳልፎ ለባእዳን ይሰጣል። ወጣት ሴቶችንና ወንዶችን ለግርድናና ለአሸከርነት የመላኩ የድለላ ሥራም ህወሃቶች ባቋቋማቸው ድርጅቶች ተካሂዶ ከዚህ ንግድ በተገኘው ገንዘብ ህውሃቶች ብዙ ገንዘብ አፈሱ። ወገኖቻችን ግን በአረቦች እጅ እንባቸውን በመዳፋቸው የሚሰፍሩ ሆነው ቀሩ።

ለዚህ ሁሉ መከራ እና ውርደት ያበቃን ምንድ ነው የሚል ርዕስም የሰሞኑ የመወያያ ርዕስ ሆኗል። የመከራውና የውርደቱ ምንጭ ፈርጀ ብዙ ቢሆንም ህወሃት ዋነኛው የችግሩ ምንጭ ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። በአጠቃላይ ግን ህወሃት መንግስት ነኝ ብሎ ሲያበቃ ዜጎችን ለመታደግ ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ እንኳ ቁጣቸውን እንዳይገልጹ መከልከሉ ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።ለዚህ ብሄራዊ ውርደትና መከራ በመጀመሪያ ደረጃ ሊጠየቅ የሚገባው ህወሃት እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። ህወሃት የኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆንን የመረጠ የጠባብ ዘረኞች ቡድን ነው። ዜጎቻቸን እንዲህ ላለው ጉስቁልናና ውርደት እንዲጋለጡ ያደረጋቸው ህወሃት መሆኑን መያዝ ለነፃነት ለሚደረገው ትግል አንዱ አካል ነው።

የተከበራችሁ ወገኖቻችን፤

በሳውዲ አረቢያ የሚሰቃዩ ዜጎችን በተመለከተ ህወሃቶች ምንም ተቆርቋሪነት ያሳዩበት ሁኔታ እንዳልታየ ታውቃላችሁ።ለወገን ተቆርቋሪነት ከህወሃቶች የሚጠበቅ ስላልሆነ እኛ አንደነቅም። አስቀድመው በገንዘብ አሳልፈው ለሸጧቸው ዜጎች ይቆረቆራሉ ብሎ መጠበቅ የህወሃቶችን ባህሪይ ካለመረዳት የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን ህወሃቶች ዜጎች ማኩረፊያ አገር እንኳን እንዳይኖሯቸው የሚያሴሩትን ሴራ ለመረዳት ካለመፈለግ የሚመነጭም ጭምር ነው። ወደ አረብ አገር የተሰደዱም ሆኑ በሌሎች አገር በስደት ላይ ያሉ ዜጎች በከፋቸው ግዜ ተመልሰው የሚገቡበት ሥፍራ አላቸው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ በኢትዮጵያ የለም። ጉራፈርዳ እና ቤንሻንጉል አገርህ አይደለም ተብሎ የተባረረ ወጣት መግቢያው የት ነው ? ከዚህ ሥፍራ ወደ ሳውዲ የተሰደደ ወጣት መመለሻው ወደየት ነው ? በዚያች አገር ድንጋይ ለመፍለጥ እንኳ የኢሕአዴግ አባል እንዲሆን በሚገደድበት አገር ምን አገር አለኝ ብሎ ነው የከፋው ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሰው? አዎን ኢትዮጵያዊያን ማኩረፊያ አገር የሌለን ከርታታ ዜጎች እንድንሆን ተደርገናል።አገር ያሳጡንም ህወሃቶች ናቸው እንጂ ሌላ ማንም አይደለም።

እንግዲህ ምን ይደረግ?

ይሄ ጥያቄ ግልጽና ቀላል መልስ አለው።አምርሮ መነሳት። ህወሃቶች በአዲስ አበባ ላይ ወንድ ልጅን አስገድደው ግብረ ሶዶም እንዲፈፀምበት ሲያደርጉ ሰምቶ “እነዚህ ምን ዓይነት አረመኔዎች ናቸው” ማለት ብቻ በቂ አይደለም።ለአረመኔ የሚገባውን ቅጣት ለመስጠት የአያቶቻችንን ጋሻና ጦር ማንሳት ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ነው። በሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ የቆየውን ውርደት እንምባ ብቻ የሚያስቆመው አይሆንም። እንዲህ የአረብ መቀለጃ የሆነውን ማንነታችንና ክብራችንን አስመልሰን አንገታችንን ቀና አድርገን በአርብ ጎዳናዎች ላይ እንደቀድሞው ዘመን በኩራት እንድንመላለስ የአያቶቻችንን ትጥቅ ከተሰቀለበት አውርደን መታጠቅ ግዴታችን ሁኗል።

ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ውስጥ ያለን ኢትዮጵያዊያን በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ውርደት ብሄራዊ ውርደት ነው እንላለን። ከዚህ በላይ ሌላ ብሄራዊ ውርደት የለም። ለዚህ ውርደት ያደረሰንም ህውሃት ነው። ህወሃት እስካለ ድረስ ብሄራዊ ውርደታችን ይቀጥላል እንጂ አይሻሻልም። እኛ የሚደርስብንን ውርደት ለማስቆም አምርረን ተነስተናል። እኛ እንዲህ ተዋርደን መኖርን ከቅድሞዎቹ ኩሩዎች አያቶቻችን አልተማርንም።እኛን ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ህወሃቶች አንገታችንን አስደፍተው አዋርደው አይገዙንም። አያቶቻችን ለነፃነታቸው እና ለአገራቸው ክብር ሲሉ በቆሙበት በጀግኖች ሥፍራ ለመቆም መንገዱን ጀምረናል። ከእንግዲህ ወዲያ ከዚህ ጉዞ የሚያቆመን ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል የለም። ለእኛ ነጋሪት ከተጎሰመ ቆይቷል እኛ የነጋሪቱን ድምፅ በሰማን ግዜ ሳናቅማማ ተነስተናል።

እናንተስ ሳትቅማሙ ለመነሳት የነጋሪቱን ድምፅ ሰምታችኋል ? ከወደ ሳውዲ የተሰማው ያ የሲቃ ጩኸት፤ ያ ሮሮ፤ ያ እንምባ አስደንጋጩ የነጋሪት ድምፅ ነው። ከዚህ ድምፅ በኋላ ፋኖ ይሠማራል እንጂ አያለቅስም።ማልቀስ የናቁንና ያዋረዱን እንዲያከብሩን አያደርግም። ነጋሪቱ ከተጎሰመ በኋላ አገሬን፤ ክብሬን የሚል ተነስቶ ያያቶቹን ጋሻና ጦር ያነሳል እንጂ እንዲያው ዝም ብሎ አያጉረመርምም።አገር ተዋርዳ፤ ህዝብ ተበደሎ ዝም ብሎ ተንጋሎ የሚተኛ ካለ ይህን ብሄራዊ ውርደት ካመጡ ቡድኖች በምን እንደሚለይ ራሱን ይጠይቅ። አበቃን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!!