0
Posted November 30, 2013 in Amharic news
 
 

አገር ማጣትንና ጥቃትን በኢሳት እንመክት !! እንግዳሸት ከኖርዎይ


አካኪ ዘራፎች

ምን ተሠራ ባዮች

እንዴት ተደፈርን እነ’ ትት ሰዎች

እንዴት ከረማችሁ – ዉላችሁ አደራችሁ ?

ትዕዛዝ የምትሰጡ – እናንት ግን የላችሁ

ምን ተሠራ ባዮች – ህዝብ የከሰሳችሁ

ክፍያ ሳትከፍሉ – ሰው የቀጠራችሁ

እጃችሁ ኪሳችሁ – የማይገባላችሁ

እትትን…እትትን ! ቀድማችሁ ያጮሃችሁ ፡፡

እንዴት ከረማችሁ ?

 

ኢሳት ባይኖር  በየአረቡ አገር በወገናችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ማን ያሰማለት ነበር ?

ኢሳት ያንን ጣዕር ባያሰማ ኖሮ የወገንን ብሶት ለማስተጋባት ስር ነቅሎ የወጣው ህዝብ ከየት ይሰማ ነበር ?

ኢሳት ባይኖር ኖሮ የወያኔዎችን ዘረፋና ፣ አገርን ሸንሽኖ ለአረብና ፣ ለህንድ፣ መሸጥ ማን ለህዝባችን ያጋልጥ ነበር ?

ኢሳት ባይኖር ኖሮ በመረጃ እጦት ምክንያት ፣ የሚንገላታውን ህዝባችንን ማን ይደርስለት ነበር ?

ብዙ ፥ ብዙ ጥያቄዎችን መደርደር ይቻላል ፡፡ ነጻነትን ለማግኘት ፣ የግድ ጦር ሜዳ መዝመትን አይጠይቅም ፡፡ በተለይ ደግሞ በውጭ አገር የሚኖረው ዜጋ ፣ አገር ቤት ለሚደረገው ትግል አጋዥ ኃይል እንጂ ፣ ወሳኝ ሃይል አይደለም ፡፡የዲያስፖራው ትግል ፣ በአቅም ግንባታ እና በማቴሪያል እንዲሁም በገንዘብ እገዛ ላይ ብቻ የሚያነጣጥር ነው ፡፡ የአገራችንን ህልውናና ሉዓላዊነትን ካጣንበት 23 ዓመታት ወዲህ ፣ ኢትዮጵያውያኖች አንድ የተሳካልንና ፣ የገነባነው ተቋም ቢኖር ኢሳት ብቻ ነው ፡፡

ብዙዎችን ድርጅቶች ገንብተን አፍርሰናል ፡፡ በብዙዎች ድርጅቶቻችን ላይ ተካሰናል ፡፡ እርስ በራስም ተረጋግመናል ፡፡ ይህን ጠንካራ ኢሳት የተባለ የጋራ ተቋማችንን እንኳ ለማፍረስ ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም ፡፡ አፍንጫው ድረስ በቢልዮኖች ዶላር ዘረፍና ፣ በምዕራባውያን እርዳታ ፣ እንዲሁም በቻይና የማፈኛ ሞገድ የሚረዳውን የዘንዶ መንግሥት እየተንገልታም ቢሆን እየወደቀና እየተነሳ ለህዝባችን አይንና ጆሮ ሆኖ የሚታደገው ኢሳት ነው ፡፡ ጠላቶቻችንና ኃላፊነታቸውን መወጣት ያቃታቸው ፣ በህሊና ወቀሳ የሚንገላቱትን ጨምሮ ኢሳት የእነ ገሌ እግሌ ነው                በሚል ክስ የሚረግሙትን ሁሉ ተቋቁሞ እነሆ እዚህ ደርሷል ፡፡ በእግሩ ቆሞ ወገንን እንዲታደግ ለመሰረቱት ወገኖች ምስጋና ይግባቸውና ፣ ኢሳት እንኳን የእነገሌ ፣ ድሮ የመላዕክት አለቃ ሆኖ ክስልጣኑ የተባበረው የዲያብሎስም ቢሆን ለህዝባችን መረጃ እስከሰጠ ድረስ የማንደግፍበት ምንም ምክንያት የለም ፡፡

አሁን ከፊታችን አንድ የአደራ ግዝት አለብን ፡፡ ኢሳት የኔ ነው የሚለውን አዲስ ራዕይ ከግብ ለማድረስ ፣ ሁላችንም ነጻነት ወዳድ ዜጎች ከኢሳት ጎን በጋራ መቆም አለብን ፡፡ ባለፈው ሁለት ሳምንት ኖርዌይ፣ አንድ አዲስ ወጣት ኃይል ኢሳትን የሚያስተዳድር   ዲሞክሪያሳዊ በሆነ መንገድ መርጧል ፡፡ የኖርዌይ ኢትዮጵያዊ ከአንዴም ሶስት ጊዜ ከዓለም ግምባር ቀደም ሆኖ ኢሳትን አኩሪ በሆነ የገንዘብ መጠን አጠናክሯል ፡፡ ኢሳት የኢትዮጵያውያኖች አልጀዚራ ይሆናል ተብሎም ቃል የተገባው እዚሁ ኖርዌይ ስለሆነ ፣ ይህ መሃላችን መውደቅ የለበትም ፡፡ በተቻለን መጠን አዲሶቹን የኢሳት አመራሮች ከጎናቸው መቆም አለብን ፡፡ በአዲስ አወቃቀርና በአዲስ ቃል ኪዳን ይህን ኃላፊነታቸውንም ይወጣሉ ብለን ሁላችንም እምነት ማሳደር አለብን ፡፡

በእስከዛሬው ተሞክሯችን የኢሳት እረጂዎች በተለያየ የአደረጃጀት ስልት የተቧደኑ ነበሩ ፡፡ አደባባይ ወጥቶ ከሚረዳው ውጭም በህቡም የሚረዱ ወገኖች ጭምር የተሳተፉበት ነበር ፡፡ ይህ ሁኔታ አሁንም በአዲሱ አመራር ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ ፡፡ ኢሳት የኔ ነውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ኖርዌይ ውስጥ ቁጥሩን ከፍ እንደምናደርገው ምንም ጥርጥር የለኝም ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከዚህ በፊት የኖርዌይን ኢሳት ባመራርና በማጠናከር የሠሩትን ወገኖች እያመሰገንኩ፣ ለአዲሶችም አመራሮች ከጎናቸው እንደምንቆም አበክረን እንገልጻለን ፡፡ ከላይ ያለችው ግጥሜ ምንም ለአገር ሳያበረክቱ ትችት ለሚያዥጎደጉዱት ወገኖች እንጂ ፣ በተናጠል ያተኮረችባቸው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የሉም ፡፡

ኢሳት የኛ አልጀዚራ ይሆናል !