0
Posted October 26, 2013 in News
 
 

ታንኮች የህዝብን ጤንነት አይጠብቁም የወያኔን ስልጣን ዘመን እንጂ


አሰፋ ዘለቀ /ሃሽታድ/ ከኖርዌይ

ከጥቂት ቀናቶች በፊት 12 October 2013(እአአ) በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ስር የሚገኘው የአገሪቱ ብቸኛ የአስክሬን ምርመራ ክፍል የምርመራ አገልግሎቱ እንዳቋረጠ ሰምተናል ደግሞም ከተለያዩ ድህረ ገጾች አንብበናል የገዥው ፓርቲ ልሳን እንደሆነ የሚታወቀው ፋና FM ሬዲዮ ደግሞ ጥቅምት 13፣ 2006 በቀትር የዜና እወጃው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከትናንት 10 ሠዓት ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ የሆስፒታሉ ታክሚዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አረዳን፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ማለት የኤሌክትሪክ ሀይሉ በመቋረጡ የቀዶ ጥገናና ጽኑ ህሙማን ታካሚዎች፣ ጠቅላላ ቀዶ ጥገና እና ድንገተኛ ቀዶ ጥገና ህክምና የሚሰጥባቸው ክፍሎች እንዲሁም ያለ ጊዜያቸው የተወለዱና ሙቀት የሚፈልጉ ህጻናት ሙቀት የሚያገኙባቸው ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመው እንደነበር እና የኤሌትሪክ ሃይል በመቋረጡ የተነሳ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ለነዚህ ከሞት አፋፍ ለደረሱና በተፈጥሮ መተንፈስ ላልቻሉ ህሙማን የህክምና ባለሙያዎቹ ዓየር በእጃቸው እየጨመቁ እንደሰጡ ተነገረን::

በሌላ ዜና ድግሞ 17 October 2013 (እአአ) የአስትሪየም ሳተላይትና HIS የተባለ የባህር ላይ መርከብ ጥምር መረጃ ሰብሳቢ እንዳመለከተው በመስከረም ወር ከዩክሬን ኦክታያብርስክ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ ታንኮች መግባታቸው ታውቋል፡፡ ወያኔ/ህዋህት በቆየባቸው 22የአገዛዝ ዘመናት ለጦርመሳሪያ ግዢ እና ለወታደራዊ አገልግሎት የሚያወጣው ወጪ የትዬለሌ እጅግ በጣም ብዙ እንደሆነ ይታወቃል ለምሳሌ ያህል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2004 ዓ.ም. ዕቅድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳው ጥያቄ በሚዲያ አውታሮች ሲሰራጭ የነበረውንና ኢትዮጵያ ከዩክሬን ሁለት መቶ ታንኮችን በአንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የመግዛቷ ጉዳይ የማይቀር መሆኑንም ለፓርላማው አረጋግጠዋል፡፡ ስለታንኮቹ መገዛት ለቤቱ የሰጡት ማብራሪያ ግን እንደተለመደው በፀጥታ ሲያዳምጡ የነበሩትን የምክር ቤት አባላት ፈገግ ያሰኘ ነበር፡፡ ‹‹አሁን በግልጋሎት ላይ ያሉት ታንኮች በዚህ ምክር ቤት ከሚገኙት አብዛኛው አባላት በላይ ዕድሜን ያስቆጠሩ ናቸው፤›› ሲሉ ያብራሩት አቶ መለስ፣ አዳዲሶቹ ታንኮች ርዝመት ያለው ርቀትን መሸፈን አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹T-72›› የተሰኙት እነዚህ ዩክሬን ስሪት ታንኮች ወደ ጦር ሜዳ ለማጓጓዝ ተጨማሪ ተሽከርካሪ የማይጠይቁ መሆናቸውንና ወደፊትም ያረጁ ታንኮችን በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የመተካት አቅጣጫ እንደሚኖር ጨምረው አብራርተዋል፡፡ ሆኖም ግን በመዲናዋ አዲስ አበባ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሆስፒታሎች ግን ትኩረት ተነፈጒቸዋል በ22 አመታት ውስጥ አንድ የረባ መጠባበቂያ ጄኔሬተር አለመኖሩ እንዲሁም ለአስክሬን ምርመራ በቂ ባለሙያ እንዲኖር ወይንም እንዲሰለጥን አለመደረጉ የወያኔ ባለስልጣናት ለኢትዮጲያ ህዝብ ያላቸውን ግዴለሽኝነት የሚያሳይ ነው::እንዲሁም ከመላው የኢትዮጲያ ህዝብ ታክስ (ቀረጥ) የሚጣለውና የሚሰበሰበው ለጠቅላላው ሕብረተሰብ ጥቅም ነው፡ታክስ (ቀረጥ) እየከፈለ ያን ጥቅም ህብረተሰቡ የማያገኘው ለምን ይሆን ? ከጥቂት አመታት በፊት ለ200 ታንኮች ግዢ 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው የተከፈለው 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ምንያህል ነው? ይህ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ 17 ቢሊዮን ብር ወይንም 17, 000,000,000.00ብር በላይ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ለታንኮቹ የወጣው ገንዘብ 17, 000 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ወይም ወደ 5, 500 የሚጠጉ የጤና ጣቢያዎችን መገንባት ወይንም ብዙ ሺ ጄኔሬተሮች መግዛት እንዲሁም ብዙ ባለሙያዎች ማፍራት ይቻል ነበር።

ቅድሚያ ለጦር መሳሪያ የአገዛዝ ህልውናችን የሚጠበቀው በጦር መሳሪያ እንጂ የህዝብ ጤና እና ሰብአዊ መብት በማክበር አይደለም የ ሚለው ወያኔ በአፍሪቃ በወታደራዊ ብቃት የመሪነት ደረጃ ላይ ያለ ሠራዊት መገንባቱ ሙባረክንም ሆነ መንግስቱ ኃይለማሪያምን እንዳላዳናቸው ሊረዳ አንዳልተቻለው የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው ስለሆነም በህዝብ ገነዘብና ህይወት ህልውናውን ላማቆየት እና እድሜውን ለማራዘም የሚፍጨረጨረዉን ወያኔ/ህዋሃት የአገዛዝ ዘመኑ አብቅቶ ፍትህ እኩልነት ነጻና ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር እስከሚመሰረት ትግላችን ይቀጥላል::

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!