0
Posted April 10, 2013 in News
 
 

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት እንዲነሳ ግፊት እያደረገ ነው ተባለ


ዘረኛውና ለጥፋት የቆመው የወያኔ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተከተለ ያለው ፖሊሲ ወደ ዘር ግጭት ሊያስገባ እንደሚችል በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሁር ለዝግጂት ክፍላችን በኢሜል በላኩት መል እክት ገለጡ። እኝሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ምሁር እንደገለጡት የወያኔ አገዛዝ ከረጂም አመታት ጀምሮ በአማራው ህዝብ ላይ የነበረውን ቂምና ጥላቻ በተለያዩ ጊዚያቶችና በተለያዩ መንገዶች ዘግናኝ ጥፋቶችን ሲያደርስ የቆየ መሆኑ ሳያንሰው ሰሞኑን እየፈጸመ ያለው ድርጊት ደግሞ ችግሩን ወደተባባሰ ደረጃ የሚያደርስና የእርስ በርስ ግጭትም ሊያስነሳ እንደሚችል ያላቸውን ከፍተኛ ስጋት ገልጠዋል። ይህ የወያኔ ድርጊት አዲስ ነገር ሳይሆን ከሃያና ሰላሳ አመታት በፊት የነበረው እቅድ አካል ነው ያሉት እኚሁ ምሁር፣ ኢትዮጵያዊያን ሁኔታውን በንቃትና በጥንቃቄ መከተል ይገባቸዋል፣ የወያኔንም ተንኮልና መርዘኝነት በትንቃቄ ሊዋጉት ይገባል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ5 እስከ 10 ሺ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ተፈናቅለው ወደ መጡበት የትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ የዘረኛ አገዛዝ ተግባርና ድርጊት ኢትዮጵያውያንን ማነጋገሩን ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለኤቪዝን ኢሳት ያነጋገራቸው የተለያዩ የሲቪክ ተቋማት እና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንዲሁም ታዋቂ ጋዜጠኞች ድርጊቱን በመኮንን ኢትዮጵያውያን በቃ ሊሉት እንደሚገባ እየመከሩ መሆናቸውን ዘግቧል።

ኢሳት እንደዘገበው በአገር ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉት የሲቪክ ተቋማት መካከል የባለራእይ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር የሆነው ወጣት ሀብታሙ አያሌው፣ የብሄር ፖለቲካ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያን ሊበታትናት እንደሚችል ገልጾ፣ በኢትዮጵያዊነት መልክና ቅርጽ የተፈጠረውን ዜጋ መልሶ በመጎተት ወደ ጎሳ ቋጥኝ ማስገባት በልዩነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር መመስረት መሆኑን ተናግሯል። ወጣት ሀብታሙ የብሄር ፖለቲካው ችግር አገሪቱን ለመበታተን ይዳርጋታል በሚል ሲሰጥ የነበረው አስተያየት አሁን ፊት ለፊት እየመጣ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊነሳ ይገባዋል ማለቱን ገልጧል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መሆኑን የጠቀሰው ኢሳት ፣ ተመስገን አማርኛ ተናጋሪዎች ከአብዛኛው ክልሎች እንዲወጡ መደረጋቸውን አስታውሷል። ካራቱሬን የመሳሰሉ ድርጅቶ ሀብት እንዲያፈሩ ሲፈቀድላቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ግን ይህን መብት ተነፍጓቸዋል ። አደጋው ዛሬ የአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዜጋ ላይ የሚደርስ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ ተፈናቃዮች ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ፣ ነግ ለእኔ ተብሎ ድርጊቱ ሊወገዝ ይገባል ማለቱን ዘግቧል።

ከጉራ ፈርዳ የተፈናቀሉ አማርኛ ተናጋሪዎች ከ1 ሺ ገጽ በላይ ያለው ማስረጃ ለመለስ ዜናዊ አቅርበው እንደነበር ያስታወሰው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ መለስ መልስ ሳይሰጥባቸው በመሞቱ እሱን የተኩትም በእጅ አዙር ተመሳሳይ ፖሊሲ እየተገበሩ መሆኑን ገልጿል ብሏል ኢሳት። ለሁሉም ድርጊት ህወሀት ተጠያቂ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ የአማራውን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው ብአዴንም ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ መግለጡን ኢሳት ዘግቧል።