0
Posted March 28, 2013 in Amharic news
 
 

የዘገየው አብዮት (ተመስገን ደሳለኝ)


‹‹አረብ ስፕሪንግ››ን ተከትሎ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖለቲካ ተንታኞች በዘርፈ ብዙ ቅሬታ በተሞላችው ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነገር መከሰቱ አይቀሬ እንደሆነ ደግመው ደጋግመው መተንተናቸው ይታወሳል፡፡ ለድምዳሜያቸው ገፊ ምክንያት አድርገው ከወሰዷቸው ችግሮች ውስጥ ስርዓቱ ለሁለት አስርታት በስልጣን ላይ መቆየቱ፣ አስከፊ ድህነት መስፈኑ፣ የስራ አጥ ቁጥር ማሻቀቡ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ክብር አልባ መሆናቸው፣ የፍትህ እጦት… ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው የበዛ ምሁራኖች እነዚህ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ ካላገኙ አብዮት ወደ ሚያቀጣጥል ‹‹ካምሱር››ነት ለመቀየራቸው የተለያዩ ሀገራትን ታሪክ ጭምር ጠቅሰው በርካታ ፅሁፎችን አስነብበዋል፡፡ የሆነ ሆኖ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን መነቃቃት ለማደብዘዝ ስርዓቱ ራሱን ለተጋነነ ወጪ መዳረጉ ይነገራል፡፡ በተለይም የደህንነት ተቋሙን፣ መከላከያ እና የፖሊስ ሠራዊትን ለማጠናከር የሀገር ሃብት ባክኗል፡፡

ጋዜጦችን እና ማህበራዊ ድረ-ገፆችን ማፈን፣ አባላትን ማብዛት፣ ካድሬዎቹ በየመንደሩ ሰርገው በመግባት ጥቃቅን እንቅስቃሴዎችን ሳይቀር እየተከታተሉ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ባለፉት ሁለት ዓመት ዋነኛ ስራው ከማድረጉ በተጨማሪ ግዙፍ ‹‹ፕሮጀክቶች››ን አዘጋጅቶ እንደማስቀየሻ ለመጠቀም የገባበት እዳ ሸክሙን ቢያበዙበትም፣ ‹‹እሳት ማጥፊያ›› ሆነው ህዝባዊ አብዮቱን አዘግይተውለታል፡፡ ይህን መደምደሚያ ለማረጋገጥ በግብፅ በአብዮቱ ዋዜማ ከታዩ የማነሳሻ እንቅስቃሴ ጋር የሚመሳሰል ቅስቀሳ በኢትዮጵያም ታይቶ ነበር፡፡ ካይሮ የሚገኘው ግዙፉ ‹‹ታህሪር›› አደባባይ በለውጥ ናፋቂዎች ከመወረሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በወጣቶች ውስጥ ለውስጥ የተላለፈ በአረብኛ ‹‹Kifaya›› የተሰኘውና በአማርኛ ‹‹በቃ›› (Enough) የሚል ትርጓሜ ያለው የቅስቀሳ ጥሪ ነበር፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ግብፃውያን አደባባይ በወጡ ማግስት ‹‹በቃ›› የሚል እንቅስቃሴ ተሞክሮ ብዙም ሳይራመድ መቀጨቱን ጠቅሶ ማመሳሰል ይቻላል፡፡

ለቱኒዚያ አብዮት ‹‹የወዲያው አነሳሽ›› (Immediate cause) የሆነው በአደባባይ ራሱን ያቃጠለው መሀመድ ቦአዚዝ የተባለ ወጣት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ የኔሰው ገብሬ በተመሳሳይ መልኩ ህይወቱ ያለፈበትን ለንፅፅር ማቅረብ ይቻላል፡፡ …በዚህ ጽሁፍም በ‹‹ዘገየው አብዮት›› ውስጥ ያልተፈቱ አንኳር ችግሮች ዛሬም መኖራቸው፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ወይም ዓመታት ‹‹አብዮት አደባባይ ጠብቀኝ›› የማለት አቅም ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ እና ከኢህአዴግ ውጪ ለለውጥ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን እናይበታለን፡፡ ጉራማይሌ-ፖለቲካ የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹የአረቡ መነቃቃት›› (The Arab awakening) እያሉ ያሞካሹት አብዮት በሰሜን አፍሪካ አገራት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹ይህ አብዮት ኢትዮጵያንም ያሰጋታል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦለት ሲመልስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹እኔ ተመሳሳይ ተቃውሞ ይነሳል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ለምን ይነሳል? ህዝብ የ5 ዓመት ኮንትራት ከሰጠን ገና 10 ወራት እንኳን በደንብ አላስቆጠረም፡፡ በድምፁ፣ በካርዱ ነው ይሄን ኮንትራት የሰጠን፡፡

ለመፈፀም ቃል የገባነውን ዳር ለማድረስ ጠዋት ማታ ደፋ ቀና እያልን ባለበት ጊዜ አስር ወር ሳይሞላ በመንገድ ላይ ነውጥ ሊያስቆመን የሚወጣው ለምንድን ነው?›› በእርግጥ መለስ ይህን ያለው በአደባባይ ነው፡፡ በጓዳ ግን ፍፁም ይህንን ሊል ወይም አምኖ ሊቀበል አይችልም፡፡ እንቅልፍ አጥቶ መስጋቱም አይቀሬ ነበር፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጠው በወቅቱ ሁሉም የፓርቲው ካድሬዎች (በትምህርት ላይ ያሉትም ጭምር ትምህርታቸውን አቋርጠው) ‹‹ወደ ህዝቡ ዘልቀው በመግባት እያንዳንዷን ብሶትና እሮሮ ሳያጋንኑም ሆነ ሳያኮስሱ እንዲያቀርቡ›› የሰጠው ጥብቅ መመሪያ ነው፡፡ የዚህ መመሪያ ዋነኛ ዓላማ ለብሶቱ አንኳር ሆነው የሚቀርቡለትን ችግሮች ከተቻለ ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠት፣ አሊያም ተጠያቂው ፓርቲው ያለመሆኑን አሳምኖ ከናዳው በማምለጥ የ‹‹ሞት ሸለቆ››ውን ማቋረጥ ነበር፡፡

የወቅቱን ጉዳይ የዘገበው የእንግሊዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣም በጊዜው አቶ መለስ ከሁልጊዜው በጠነከረ ሁኔታ ከደህንነት ተቋሙ ሰዎች ጋር በተደጋጋሚ ስብስባ ያደርግ ነበር ብሏል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የ‹‹አባይ ግድብ››ን የመሰለ ግዙፍ ፕሮጀክት ለመግንባት ቅድመ-ዝግጅቱ መጠናቀቅ ተመስገን ደሳለኝየተበሰረውም በዚያው ሰሞን የሆነው ‹‹መንግስት ለልማት ቁርጠኛ አቋም›› የያዘ በማስመሰልና ተስፋ በመስጠት ተጨማሪ ማሰቀየሻ ለማግኘት በተሰላ ጨዋታ ይመስለኛል፡፡ አቶ መለስ ህዝባዊ አብዮቱን ‹‹ገትረው ይይዙልኛል›› ብሎ የነደፋቸው እቅዶች ያለስህተት መተግበራቸውን ቅድሚያ ሰጥቶ በመቆጣጠሩ፣ በትክክልም ስርዓቱ ለሁለት አስርት ዓመትታ በስልጣን መቆየቱ የፈጠረው መሰላቸት፣ አምባገነን ባህሪው እና የለውጥ ፍላጎት ድምር ውጤት ሊያነሳው የነበረውን ህዝባዊ አብዮት ተከላክሎታል፤ ወይም አዘግይቶታል፡፡

እነዚህ ሁሉ አጀንዳዎች የተፈራውን ቁጣ ከአደባባይ ለማስቀረት ጉልበት ካነሳቸው ግን የታጠቀው ኃይል ነቅቶ ይጠብቅ ዘንድ ከደካማው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የትየለሌ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ ማዘጋጀቱ አማራጭ የሌለው የመጨረሻ መፍትሄ ነበር-ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር ለግንባሩ አዲስ አይደለም፡፡ አደጋ በአጋጠመው ወይም ባሰጋው ጊዜ ሁሉ ጉራማይሌ አቋም መያዙ የተለመደ ነው፡፡ …ህዝብ ኮንትራት ሰጥቶናል፤ የሰሜን አፍሪካን አመፅ እዚህም ሊደግሙ ሲሉ ደረስንባቸው…፡፡

በማን እጅ ነው እውነታው? ድህረ-መለስ ኢህአዴግ የቀድሞ ሊቀመንበሩ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ፣ ቀድሞ በግንባሩ ውስጥ ተጨፍልቀው የነበሩ ጥያቄዎች እና የተለያዩ ቅሬታዎች አቧራቸውን አራግፈው ጠረጴዛው ላይ የተቀመጡለት ይመስላሉ፡፡ በእርግጥም በአፍሪካ በ‹‹ህይወት›› ከሰነበቱ በጣት የሚቆጠሩ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢህአዴግ ከምስረታው ጀምሮ የሚያውቀው ብቸኛው ሊቀመንበሩ ህልፈት በኋላ ለአመታት የገነባው ጥንካሬ እየከዳው ለመሆኑ ምልክቶች ይታዩበታል፡፡ የሰውየው በድንገት ማለፍ ለፓርቲው የከፋ የሆነው ከ‹‹ውርሶቹ›› መሀል የበዛው ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ አደጋ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ለድህረ-መለስ ዘመን ክፉ ውርሶች ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ አቶ መለስ ባለፉት ዓመታት ቅራኔዎችን እና ቅሬታዎችን ያስተናገደበት መንገድ ነው፡፡

ይኸውም ህዝባዊ ጥያቄዎችን በማፈን፣ የመብት ጥሰት በመፈፀም፣ የአደባባይ ተቃውሞን በመከልከል፣ አፋኝ ህጎችን በማውጣት፣ የድርጅቱን የቡድን አመራር በአንድ ጠንካራ ሰው ቀይሮ የስልጣን እድሜውን ያራዘመበት… ስልትን አዲሱ አስተዳደርም የራሱ አድርጎ ተቀብሎታል። ሆኖም ይህ ቀመር በድህረ-መለስ ዘመንም የ‹‹አዲስ ወይን ጠጅ›› ጣም ይዞ የፖለቲካ መረጋጋትን ለማንበር የሃሳቡን ባለቤትና አስፈፃሚ ይፈልጋል፤ ወይም በግልፅ አማርኛ የመለስን መንገድ ለመከተል፣ መለስን መሆን የግድ ይላል፡፡ የግድግዳው ፅሁፍም ‹‹በድህረ-መለሱ ኢህአዴግ፣ ማነው አዲሱ መለስ ዜናዊ?›› የሚል ይመስላል፡፡

ማነው አዲሱ ‹‹መለስ››?

የአረብ ሀገራት መነቃቃት ከተከሰተ ሁለት አመት አልፎታል፡፡ በቱኒዚያ፣ በግብፅ እና በሊቢያ የስርዓት ለውጥን አምጥቷል፡፡ ሞሮኮ፣ኳታር እና የመንን ደግሞ የፖለቲካ ማሻሻያ ያደርጉ ዘንድ አስገድዷቸዋል፡፡ ኢህአዴግም ምንም እንኳ ከአብዮቱ ጋር በተያየዘ ባይሆንም የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ ለውጡን ተከትሎም በአንድ ሰው መዳፍ (ዕዝ) ስር የነበረው ትልቁ የፖለቲካ ስልጣን ተመንዝሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና ለሌሎች ሶስት ምክትሎች ተከፋፍሏል፡፡ ችግሩ የ‹‹ስልጣን ምንዘራው›› አይደለም፤ ችግሩ አቶ መለስ ‹‹ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ስልጣን ልቀቅ›› ብሎ እንዳያምፅበት ለማድረግ የተጠቀመበትን ቀመር ሙሉ በሙሉ ሳይላምጥ መዋጡ ነው፡፡ ጥያቄውም ዛሬስ ተመሳሳይ መንፈስ ቢነሳና ተተኪዎቹ የመለስን ስልት ለመተግበር ከመረጡ ይሳካላቸዋልን? ወይስ አዲስ አማራጭ ይኖራቸው ይሆን? የሚለው ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ መልሱ ያለው ባልተፈታው ቋጠሮ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ ‹‹አዲሱ መለስ›› ማን ነው?

የደኢህዴኑ ኃይለማርያም ደሳለኝ? የህወሓቱ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል? የብአዴኑ ደመቀ መኮንን? ወይስ የኦህዴዱ ሙክታር ከድር? በአናቱም ኢህአዴግ በድህረ-መለስ ከአዲስ ተግዳሮት ጋር ተፋጧል፤ ከውስጥ ቅራኔ ጋር በተያየዘ፡፡ በህወሓት በኩል በአመራሩ (በእነ ደብረፅዮን እና አዜብ መስፍን) መካከል፣ እንዲሁም የካድሬው ያልተመለስ ጥያቄ ሲጠቀስ፣ ኦህዴድም በተመሳሳይ መልኩ በራሱ የአመራር አባላት ውስጥ ያቆጠቆጡ ልዩነቶች እየተመዘዙበት ከመሆኑ በተጨማሪ፤ ‹‹ከኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች አብላጫ ህዝብ ስለወከልን ስልጣን በቁመታችን ልክ መያዝ አለብን›› የሚለው የታችኛው ካድሬ ግፊት ተጠቃሽ ነው፡፡ (ይህንን ጥያቄ የኢህአዴግ የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ለዝቦ የሚሰማ የኦነግ ድምፅ›› ሲሉ ያጣጥሉታል) ሌላው ኢህአዴግን እያንገዳገደው ያለው ብዙ የተነገረለት ‹‹የመለስ ውርስ›› ያዘለው አደጋ ነው፡፡

ምክንያቱም አቶ መለስ የለውጡን መነሳሳት በማፈን፣ የስልጣን እድሜው ያለስጋት ይረዝም ዘንድ፡- አመፅ ቀስቃሽ ያላቸውን ማህበራዊ ድረ-ገፆች፣ የአሜሪካ እና የጀርመን ድምፅ የሬዲዮ ስርጭት፣ አልጀዚራ እና ኢሳትን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን ለማፈን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማባከኑ በፍጥነትሊስተካከል የማይችል የኢኮኖሚ ክስረት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ እንዲሁም አቶ መለስ ጀምሮት የነበረው የተጋነነ የመከላከያ፣ የደህንነት እና የፖሊስ ሰራዊት ግንባታም ለአዲሱ አስተዳደር አቅሙን ያልመጠነ ከባድ ሸክም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

እናም ዛሬ ከዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግር እንደብልህ ‹‹ቼዝ›› ተጫዋች በ‹‹ጥበቡ›› የተሻገረ ብቸኛው ሰው አቶ መለስ አልፎ፣ የጨዋታውን ህግጋት እምብዛም ባልተረዳ ቡድናዊ አመራር ተተክቷል፡፡ ከመተካካቱ ጋርም የቀድሞው አስተዳደር የገባቸው ዕዳዎች አብረው ተላልፈዋል፡፡ አዲሱ መንግስትም በይፋ ስለእነዚህ ችግሮች (የመለስ ውርስ) በአደባባይ ተናግሮ ባያውቅም፣ አቶ መለስ የአረብ ሀገራትን መነቃቃት ተከትሎ ያጉረመረመበትን የህዝብ ቁጣ ለማክሸፍ በድፍረት የተነከረበት ዕዳ፣ በተቃራኒው ተተኪው አስተዳደር በራሱ ላይ መከራን ሊጠራበት የሚችል ‹‹ሟርት›› መሆኑ ይጠፋዋል ማለት ግብዝነት ይመስለኛል (በነገራችን ላይ አዲሱ አመራር በመጪዎቹ ጊዜያት ከዚህ አይነቱ አደጋ አምልጦ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም፣ የፖለቲካውን ችግሮች በሙሉ የአቶ መለስ ኪሳራ በማስመሰል እንደ‹‹ማስቀየሻ›› ለመጠቀም መሞከሩ አይቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡)

የሆነ ሆኖ በግሌ አዲሱ አስተዳደር ‹‹መውጫ በር›› ሊያስገኝለት የሚችለው ብቸኛ አማራጩ ከመለስ ስነ ልቦና ራሱን ነፃ ማውጣት ከቻለ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም አቶ መለስ በስልጣን ዘመኑ ሙሉ ከተቀናቃኞቹ ጋር ‹‹ሰጥቶ በመቀበል›› መርህ ላይ የተመሰረተ ድርድር (ንግግር) በጭራሽ አድርጎ ካለማወቁ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ተተኪዎቹ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው መጓዝ (በእኩል ጠረጴዛ ለሚደረጉ ንግግሮች ራሱን ማሳመን) ከቻለ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር በጉልበትና በብልጠት አንድ አድርጎ በማሰር ተሸክሞ ያዘገየውን አብዮት ሙሉ በሙሉ የማስቀረት ዕድሉ ገና ከእጃቸው አልወጣም፡፡ በትህትና አልረፈደም እንደ ማለት ነው፡፡ በአናቱም ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ‹‹መልካም ሰው ነው›› የሚለው ማሞካሸት ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ ከሆነ የጥንት ፈላስፎች በአስተምህሮታቸው ‹‹ጥሩ ሰው፣ ጥሩ አስተዳደር ይሆናል›› (The good man be a good ruler) የሚሉት ምን ያህል ይሰራ እንደሆነ ለማረጋገጥ ብዙ ላንጠብቅ እንችላለን፡፡ በተረፈ ስርዓቱ በለመደው ትምክህት፣ አሊያም በግንዛቤ ችግር ‹‹ነገም ዝምታው እንዳረበበ፣ አደባባዩም በፀጥታ እንደተዋጠ፣ ስልጣኔም እንደተረጋጋ መሽቶ ይነጋል›› በሚል ቀቢፀ-ተስፋ ከፖለቲካ መፍትሄ ከታቀበ ግን ታሪክ ራሷ በተቃራኒው መቆሟ አይቀርም፡፡

የዘገየው አብዮት…

እርግጥ ነው የለውጡ ባቡር ግስጋሴውን ገቶ፣ መንገድ መሀል መቆሙን የድህረ-መለሱ የኢህአዴግ አመራር አባላት አልተረዱትም ማለት አይቻልም፡፡ በተጨማሪም የአብዮቱን ‹‹ክረምት›› ያዘገዩት ሁለት ምክንያቶች መሆናቸው የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ የመጀመሪያውና ትልቁ ከላይ ያየነው የአቶ መለስ አደጋ የማሽተት ችሎታውና የቀመራቸው የመከላከያ ስትራቴጂዎቹ ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ግን ከኢህአዴግ ክብ መስመር ውጪ ያሉ ሶስት ጉዳዮች ያለመሟላት ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

በዓለማችን አብዛኛውን ጊዜ እንደታየው የአገዛዞችን አምባገነናዊ ባህሪ ተከትለው የሚከሰቱ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ረገጣዎችንም ሆነ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ድልድል ያለመኖር በህዝባዊ አብዮት ወይም በምርጫ ለመለወጥ የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ግንባር ቀደም ኃይል ነው፡፡ ነገር ግን እንደአለመታደል በኢትዮጵያ በአደረጃጀትም ሆነ በአላማ ፅናት ጠንካራ ሆኖ ይህንን አይነት ኃላፊነት ሊወስድ የሚችል የተሳካለት ፓርቲ ማየት አልተቻለም፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ‹‹በጨቋኝ አስተዳደር ውስጥ የተወለደ ደካማ ፓርቲ ውሎ ሲያድር መገፋቱ በራሱ ጠንካራ ያደርገዋል›› የሚለው ትንተናቸውም በኢትዮጵያ አውድ የሚሰራ አይመስልም፡፡ በግልባጩ ፓርቲዎቹ ከመጠንከር ይልቅ ተዳክመው ወይ ሲደበዝዙ አሊያም ታሪክ ሆነው ሲያልፉ ነው የሚታዩት፡፡

ከአንድ እጅ ጣት በታች የሚቆጠሩትና ራሳቸውን ከሌሎቹ የተሻሉ አድርገው የሚሰብኩትም ቢሆኑ እንቅልፍ በተጫነው የፖለቲካ ስራ ሲዋልሉ መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜም ገዥው ፓርቲ የራሱን አጀንዳ ‹‹ብርብራ›› አድርጎ አስክሮ እየጣለ ሲያላግጥባቸው ዓመታት እንደዋዛ ነጉደዋል፡፡ በጥቅሉ ‹‹መደራጀት›› በህግ ከተደነገገበት (ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ዓመት ጀምሮ) ምን ያህል ፓርቲዎች ተመስርተው ምን ያህሉ ከሰሙ? የሚለውን ብናይ ለዚህ ተጠየቅ አስረጅ ከመሆኑም በላይ አስደንጋጭ ዕውነት ነው፡፡ በጥቅሉ ከ‹‹አረቡ መነቃቃት›› በፊትም ሆነ በኋላ በኢትዮጵያ ስርዓቱን ለመለወጥ የሚያስገድዱ ገፊ ምክንያቶች በርካታ እንደሆኑ ቢጠቀስም ከፊት ሆኖ ሊያስተባብርና ሊመራ የሚችል ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መፈጠር አለመቻሉ ለ‹‹ዘገየው አብዮት›› አንዱ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡፪

ሌላኛው ‹‹ለህዝብ መነቃቃት›› አይነተኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው የ‹‹መብት ተሟጋቾች›› (Activist) በብዛት ያለመኖሩ እንደሆነ አብዛኞቻችንን ያስማማናል ይስማማሉ፡፡ ለተሟጋቾቹ ያለመበራከት አንደኛው መነሻ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህሉ መደራጀትን በፖለቲካ ፓርቲነት መልክ ብቻ ማየቱ፣ ለአክቲቪዝም እምብዛም ጠቀሜታ ያሌለው የጋርዮሽ ውሳኔ መለመዱ፣ የመሪና ተመሪ ግንኙነት ገዢ ልማድ ሆኖ መቆየቱ፣ ከዚህ ባለፈም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻችን ለአክቲቪዝም ባዕድ መሆናቸው… ነው፡፡ ሆኖም ሁሉንም የሚያስማማው ‹‹የመብት ተሟጋች›› (አክቲቪስት) አምባገነን ስርዓት ለመታገል አንዱ አማራጭ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በቱኒዚያ እና በግብፅ የተደረገው አብዮትም የአክቲቪስቶችን ሚና ከፍ አድርጎ ያሳየናል፡፡ በይበልጥ በግብፅ ምንም እንኳ በተበታተነ መልኩ ቢሆንም ከአብዮቱ አስራ አምስት እና አስር ዓመት በፊት ጎዳናው ላይ የሚታዩ አክቲቪስቶች መኖራቸው በአብዮቱ ዋዜማ ስርዓቱን ለመቀየር ብዙ ጉልበት አልጠየቃቸውም፡፡

ይህ ልምዳቸውም በግብፅ ተሰሚነት ያላቸውን ተቋማት ከጎናቸው ማሰለፍ አስችሏቸዋል፡፡ በርካታ ደጋፊ ያላቸውን የእግር ኳስ ቡድኖች ሳይቀር የዓላማቸው ደጋፊ አድርገዋል፡፡ ‹‹Institution of development studies›› የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋምም በጃንዋሪ 2012 ዓ.ም ‹‹The Pulse of Egypt’s Revolt›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መድበል ‹‹January 25th was that activist had successfully managed to secure the participation of the ultras youth belonging to the two key sports teams in Egypt, Al Ahly and Zamalek›› (አብዮቱ በተነሳበት ጃንዋሪ 25 ቀን፣ የንቅናቄው አንቀሳቃሽ የነበሩት አክቲቪስቶች የትላልቆቹን የግብፅ የእግር ኳስ ቡድኖች አል-ሃሊ እና ዛማሌክ ደጋፊዎችን ማሳተፍ ችለዋል) ሲል አክቲቪስቶቹ ምን ያህል እርቀት መጓዝ እንደቻሉ ለማሳየት ሞክሯል፡፡

በጥቅሉ አክቲቪዝም የተሻለ ቦታ በደረሰባቸው አገራት ራሳቸው አክቲቪስቶች ፖለቲካዊ ያልሆኑ ጉዳዮችንም ጭምር እያስጮኹ ስርዓቱ እንዲያስተካክላቸው ወይም መፍትሄ እንዲሰጥባቸው መጠየቁን ደጋግመው መተግበራቸው በቂ ልምድ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ድግግሞሽ ፍርሃትን ከመስበሩም በላይ የአክቲቪዝምን ባህል እና ተደራጅቶ መብትን መጠየቅን ያለማምዳል፡፡ ከዚህ ባሻገር የኢንተርኔት ተጠቃሚው ዜጋ ቁጥር መጨመር እና የጦማሪዎች (ብሎገሮች) መብዛት አክቲቪዝምን ባህል ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ጥናትም እንደሚለው፣ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች እየበዙ ሲመጡ መዋቅራዊ ባልሆነ እና የመንግስትን ዕውቅና በማይጠይቅ መልኩ የዜጐችን የርስ በርስ በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ተሰብስቦ መብትን የመጠየቅ የዜግነት ባህል እንዲዳብር ያደርጋል፡፡

ጉዳዩ በኢትዮጵያ አውድ ከታየ አክቲቪስቶችን ወደ አደባባይ ለማምጣት የሚያስችሉ በርካታ አጀንዳዎች አሉ፡፡ ለምሳሌም፡- የሀይማኖት ጣልቃ ገብነት፣ የደሞዝ ማሻሻያ፣ በተለያዩ ከተሞች የሚደረገው የዜጎች መፈናቀል፣ የመሬት ቅርምት፣ የዋጋ ንረት… የመሳሰሉትን አጀንዳዎች በቀላሉ ማስጮኽ ይቻላል፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ስር የሚካሄዱ ተደጋጋሚ ሰልፎች መንግስትን ተጭነው ማሻሻያ እንዲያደርግ፣ ፍቃደኛ ካልሆነም ለመለወጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በግብፅ የታየውም ይኸው ነው፡፡ ካህሊድ አሊ የተባለው ፀሐፊ “Precursors of the Egyptian Revolution” በሚለው ፅሁፉ እንደሚያትተው፣ ከታህሪር አብዮት በፊት ባሉት ዓመታት ከፖለቲካ ውጪ የማህበረ- ኢኮኖሚና ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን ያነገቡ ሰልፎች ቁጥር መብዛት አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እኒህ ሰልፎች ማህበረሰቡን በማነቃቃት መብቶቹን ለመጠየቅ በግድ በፖለቲከኞች መደራጀት እንደማይኖርበት እንዲያምን አድርጎታል፡፡ አጥኚውም ‹‹ካለነዚህ ሰልፎች አብዮቱ አይሳካም ነበር›› ሲል፣ የተሳታፊዎቹ ቁጥር አነስተኝነትም ሆነ በተለያየና በተበጣጠሰ መልኩ ሲካሄዱ የነበሩትን ሰልፎች ያላቸውን ዋጋ አስቀምጧል፡፡

የሆነ ሆኖ በኢትዮጵያ በዚህ መልኩ የመታገሉ ልምድ ስለሌለ የመንግስቱ ኃ/ማርያምን አስተዳደር ለመቀየር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ለመገበር ከማስገደዱ በተጨማሪ አስራ ሰባት ዓመታትን ያህል ፈጅቷል፡፡ ከዚህ ሁሉ መስዕዋትነት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው ኢህአዴግ ደግሞ ሃያ አንደኛ ዓመት የስልጣን ዘመኑን ጨርሶ፣ ወደ ሃያ ሁለተኛው ተሸጋግሯል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ ወደ ሃያ ሶስተኛ ዓመቱ ለማለፍ እንቅፋት ይገጥመዋል ማለት ከባድ ይመስላል (ሲቪክ ማህበራት ለአክቲቪዝም ትልቅ ድርሻ ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ግን የሲቪክ ማህበራቱ ጠንክረው እንዳይንቀሳቀሱና በእግራቸው እንዳይቆሙ መንግስት በግልፅ አፋኝ ህግ እስከ ማውጣት የደረሰ በመሆኑ ማህበራቱን ለመውቀስም ሆነ ለማመስገን አስቸጋሪ ነው)

በሶስተኛ ረድፍ ለስርዓቱ መፋፋት ተጠያቂ ሆኖ የሚቀመጠው ለአንድ ማህበረሰብ አንቀሳቃሽ ኃይል ተደርጎ የሚወሰደው ወጣቱ የማስተባበርና የመምራት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ይመስለኛል፡፡ በተለይም የወጣቶች ቁጥር በሚበዛበት ሀገር ‹‹ጭቆና››ን ለተራዘመ ጊዜ የመሸከም ልምዱ አናሳ እንደሆነ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ አክሎግ ቢራራ ከአረቡ መነቃቃት በኋላ ‹‹Ethiopian fascination with Arab spring›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት ከ1983 ዓ.ም ወይም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ከአርባ ሚሊዮን የሚልቁወጣቶች እንደተወለዱ ገልፀዋል፡፡ ይህ ቁጥራዊ ውጤት ደግሞ ወጣቶቹ ከአጠቃላይ ህዝቡ ያላቸው ቁጥራዊ ድርሻ ከሰሜን አፍሪካዎቹ ሀገራት ጋር የሚመጥን ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያን ወጣት ለየት የሚያደርገው ደግሞ ለቁጣ ቶሎ የሚያነሳሱ ስራ አጥነትን በመሳሰሉ ችግሮች ስር መውደቁ ነው፡፡ በተለያዩ ሀገራት እንደታየው ወጣቶች በስራ አጥነት ለረጅም ጊዜ መቀመጡ የሚፈጥርባቸው ስነ-ልቦናዊ ቀውስ እና የወጣትነት ፍላጎትን ለማሟላት አቅም የሌላቸው መሆናቸው መንግስትን ተጠያቂ አድርገው ስርዓቱን ለመጣል ወደሚያስችል አመፅ ይገፋቸዋል፡፡ በግልባጩ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤትን ዝቅ በማድረግና በርካታ ኮሌጆችን በመክፍት፤ እንዲሁም ስደትን በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በማበረታታት በተቻለው አቅም ስራ አጡ ወጣት ወደ አደባባይ እንዳይወጣ የሚያደርጉ ስልቶችን ሲከተል ይስተዋላል፡፡

ይህ ከፍተኛ ት/ትን በስፋት የማዳረሱ ጉዳይ ለስርዓቱ ‹‹ቡምራንግ›› (በአውስትራሊያ የሚኖሩ የአቦርጂንስ ጎሳዎች ባህላዊ መሳሪያ ሲሆን፣ መሳሪያው ኢላማውን ከሳተ ተመልሶ ራሱ ተኳሹን የሚመታ ነው) የመሆን እድል እንዳለው ግን ስርዓቱ የተረዳው አይመስልም፡፡ ከትምህርት ተቋማቱ ትምህርታቸውን ጨርሰው የሚወጡት ወጣቶች ስራ-አጥ የመሆን እድል ሲገጥማቸውና ለዚህ ችግራቸውም ገዢውን ፓርቲ ተጠያቂ ማድረግ ሲጀምሩ አብዮቱን ለመቀስቀስ ይገፋፋሉ፡፡

በኢትዮጵያም እነዚህ ሁሉ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩም አሁንም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለመንግስት ተጨማሪ ዕድል የሰጠ ይመስላል፡፡ ምናልባትም የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉትና የግብፅን አብዮት ካሳኩት ወጣቶች ጋር ለንፅፅር ሲቀርብ የእርቀቱ መስመር የልዩነቱን ጥልቀት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግብፃውያን ወጣቶች የሆስኒ ሙባረክን አስተዳደር ለመቀየር በጎዳናው ላይ ተሰባስበው ሲያበቁ ‹‹Our people, join us, freedom is for you and us›› (ህዝባችን ሆይ ከእኛ ጋር ተሰለፍ፣ የሚፈነጥቀው ነፃነት ለእኛም ለአንተም ነውና) ሲሉ ከመዘመር ያገዳቸው አንዳች ኃይል አልነበረም፡፡

የወንድ በር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር ‹‹መሬት አንቀጥቅጥ›› ለሚሉት አይነት ተቃውሞ በር የዘጋ መሆኑን የሚናገሩ ምሁራኖች መከራከሪያቸው ስርዓቱ በብሄር ተኮር ፖለቲካ የተቃኘ መሆኑን እና የሀይማኖት ልዩነትን ማጎኑን ነው፡፡ በእርግጥ ራሱ መንግስት የሃይማኖት ልዩነትንም ሆነ የብሄር ፖለቲካውን ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ሲያውለው ማየቱ አዲስ አይደለም፡፡ ይሁንና እንዲህ አይነት ብልጣ ብልጥነትን ተማምኖ ዛሬም በትምክህት መቀመጡ ለታሪክ ስህተት መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ኢህአዴግ ፈቀደም አልፈቀደም የኢትዮጵያ ጎዳናዎች ለውጥን በሚጠይቁ ወጣቶች የሚጥለቀለቁበት ቀናት ያን ያህል የተራዘመ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ሊነሳ የሚችለው የአብዮትን ባህሪ ዛሬ ለመተንበይ አስቸጋሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ (እንደየአገዛዙ ባህሪ የሚወሰን በመሆኑ) የሊቢያን ወይም የሶርያን የመሰለ ተቃውሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የሀገራቶቹ ተሞክሮ እያሳየን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ያለው አገዛዝ የቱንም ያህል የከፋ ቢሆን በዚህ መልኩ ለመቀየር መሞከሩ የባሰ ችግሩን ማባባስ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የግብፅና የቱኒዚያ የለውጥ መንገድ ግን ፍፁም ሰላማዊ እና ህግን ያከበረ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የግድ የገዥው ፓርቲን ቡራኬ እስኪያገኝ መጠበቅ ያስፈልጋል ብዬ አላምንም፡፡ ሰላማዊው የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮትንም ወደኋላ ተመልሶ መፈተሹተገቢ ይመስለኛል፡፡ በግሌ የትኛውም አይነት አብዮት ህዝብን አነሳስቶ ወደ አደባባይ ከማውጣቱ በፊት ስርዓቱን ራሱ ለለውጥ ቢያመቻች የተሻለ መሆኑን እመክራለሁ፡፡

በቀላሉም አፋኝ ህጎችን ማንሳት፣ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ ለህግ የበላይነት መገዛት ለገዥው ፓርቲ ዋጋ የማያስከፍል ከመሆኑም በተጨማሪ በርካታ ጥፋቶችን ይታደጋል፡፡ አሊያም ከኢህአዴግ አለመረጋጋት፣ አዲሱ መለስ ለመሆን በሚፈጠረው መተጋገል የሚከሰተውን ድክመት እና የመሳሰሉት የወቅቱ ፖለቲካ መገለጫዎች የልብ ልብ ሰጥተውት አንዴ አደባባይ የወጣ ወጣት ምንም አይነት ኃይል ሊመልሰው እንደማይቻል አስቀድሞ ማወቁ ብልህነት ይመስለኛል፡፡