0
Posted March 16, 2013 in Amharic news
 
 

ፊን ፊሸር ሰላዩ ቫይረስ


ፊን ፊሸር የተባለ የስለላ የኮምፕዩተር ፕሮግራም በዓለም 25 ሀገሮች ዉስጥ መሠራጨቱንና መንግስታቱም የገዛ ዜጎቻቸዉን ለመሠለል እንደሚጠቀሙበት አንድ ጥናት አመለከተ። ኢትዮጵያ ዉስጥም በሠፊዉ ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።

የኢንተርኔት ቫይረሱ ኮምፕዩተር ዉስጥ ከገባ ግለሰቦች በኮምፕዩተራቸዉ ላይ የሚያደርጉትን የፅሁፍ የድምፅና የምስል የመልዕክት ልዉዉጦች ወደዋና መረጃ ማሰባሰቢያዉ ማዕከል ይልካል። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች RSF ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢንተርኔት ላይ የሚደረገዉን ቁጥጥር አስመልክቶ የተጠቀሰዉ የስለላ የኮምፕዩተር ፕሮግራም ሥራ ላይ መዋሉን ጥናቱን ጠቅሶ ለዶቼ ቬለ መግለፁን ዘግበናል። ዶቼቬለ ስለጉዳዩ የጠየቃቸው የኢትዮ ቴሌኮም የኮምንኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ኢትዮ ቴሌኮም በተጠቀሰው ፕሮግራም እንደማይገለገል በስልክ ተናግረዋል። አቶ አብዱራሂም ስለጥናቱ ውጤት እንደማያውቁ ገልፀው ሆኖም ፊን ፊሸር የተባለው የስለላ የኮምፕዩተር ፕሮግራም ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ውሏል መባሉን ከዕውነት የራቀ ሲሉ አጣጥለውታል።

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት RSF በያዝነዉ ሳምንትባወጣዉ የኢንተርኔት ቁጥጥርን የሚመለከት ዘገባ አምስት ሀገሮችን የኢንተርኔት ጠላት ሲል ፈርጇል። የሶርያ፤ ቻይና፤ ኢራን፤ ባህሬን እንዲሁም የቬትናም መንግስታት የኢንተርኔት መረጃዎችን ለመቆጣጠር ከሚሰነዝሩት የድረገፅ ጥቃት በተጨማሪ ዜጎችን ለመሰለል የግለሰቦችን የኢሜል መረጃ የሚያጠምዱ ፕሮግራሞችን በመጠቀም ግንባር ቀደም ተብለዋል። ከበርካታ ሀገሮች እነዚህ አምስቱ የተመረጡትም ለኢንተርኔት ቁጥጥሩ የሚጠቀሙበት ቴክኒዎሊጂ መራቀቅና በዚህ ስለላ መሠረትም ጋዜጠኞችና ዜጎቻቸዉን በማሰራቸዉ እንደሆነ የRSF የዘመናዊ መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ተመራማሪ ግሬግዋ ፑዤ ገልፀዋል። በተለይም ቻይና የኤሌክትሮኒክ መከላከያዋ ከዓለም ምናልባትም የረቀቀ ተብሎ ሲገመት ይህንኑ ቁጥጥሯን ለማጠናከር የግል ኢንተርኔት ኩባንያዎች ዜጎቿን ለመሰለል የሚረዱ ስልቶችን እንዲያቀርቡላት ማድረጓም ተገልጿል። ኢራን በበኩሏ የራሷን «ሃላል ኢንተርኔት» በሚል አቋቁማ የኢንተርኔት መረጃ ቁጥጥሯን አጠናክራለች። RSF የተራቀቀ ቴክኒዎሎጂን ሳይኖራቸዉ አምባገነን መንግስታት ዜጎቻቸዉን ለመሰለል እንደማይችሉ በማመልከት ለመጀመሪያ ጊዜ ተባባሪ የኢንተርኔት ጠላቶች ሲል የመሰለያ ፕሮግራሞችን የሚሰሩና ለሀገራቱ የሚያቀርቡ ድርጅቶችንም ስም አጋልጧል። ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት ዜጎቻቸዉን በኢንተርኔት መረጃ ልዉዉጥ ሳይቀር እንዲቆጣጠሩና እንዲሰልሉ ስልቱን እያስተካከሉ የሚያቀርቡትን አምስት የግል ኩባንያዎችም የዘመኑ «ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች» ሲል RSF ወቅሷል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በርከት ያሉ ድረ ገፆች መነበብ እንደማይችሉ ተደጋግሞ የተገለፀ ጉዳይ ነዉ፤ መንግስት በበኩሉ ወቀሳዉን ቢያስተባብልም። የጥናቱ ተባባሪ ፀሐፊ ግሬግዋ ፑዤ ከአምስቱ ሀገሮች ተርታ በዘገባዉ ኢትዮጵያ ያልተጠቀሰችዉ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንደአምስቱ ሀገሮች የተስፋፋ ባለመሆኑ እንደሆነ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ያ ማለት ግን ድርጅታቸዉ ክትትል አላደረገም ማለት አይደለም፤

«ባለፈዉ ዓመት ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን እንደተደረገ እየተካተልን ቆይተናል። ማለትም TOR የተሰኘዉ ስልት ተዘግቷል፤ የሰዎች ኢሜይል ልዉዉጥ እየሰበረ የሚበረብረዉ DPI የተሰኘዉ ፕሮግራምም ስራ ላይ መዋሉን እናዉቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ሲቲዝን ላብ የተሰኘዉ ተቋም ከቶሮንቶ አንድ ዘገባ አዉጥቷል፤ ያም ኢትዮጵያ ዉስጥም አንድ የግለሰቦችን የኮምፕዩተር መረጃ የሚያጠምድ ፕሮግራም መጠቀም መጀመሩን ይገልፃል። ተቋሙ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢንተርኔት ላይ የሚካሄደዉን ቁጥጥር የሚያረጋግጥ መረጃ አካቷል።»

ግሬግዋ ፑዤ የጠቀሱት ሲቲዝን ላብ የተሰኘዉ ተቋም ይፋ ያደረገዉ ዘገባ የግለሰቦችን መረጃ የሚያጠምደዉ የኢንተርኔት ፕሮግራም ፊን ፊሸርስ እንደሚባል ይገልፃል። እንደዘገባዉም ኢትዮጵያ በተለይም ከተቃዉሞ ፖለቲካ ቡድኖች ጋ ግንኙነት ያላቸዉ ግለሰቦችን ለመከታተል ትጠቀምበታለች።

 

ኩባንያዉ ይህን የግለሰቦችን የኢንተርኔት መረጃ የሚያጠምድ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ያዘጋጀዉ የግንቦት ሰባት አባላትን ፎቶዎች በመጠቀም እንደሆነም ዘገባዉ በመዘርዘር ምስሎቹን ያሳያል። ግሬግዋ ፑዤ፤

«ባለፈዉ የበጋ ወቅት ሲቲዚን ላብ ፊን ፊሸር የተሰኘዉ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ዉስጥ ሥራ ላይ መዋሉን ደረሰበት። የግንቦት ሰባትን «ስሙን በትክክል ብየዉ እንደሁ አላዉቅም» ምስል የያዘዉ ይህ ህገወጥ ፕሮግራም በርካታ የተቃዉሞ ፓርቲ አባላት በኢሜል አድራሻቸዉ እንዲደርሳቸዉ ተደረገ። እናም ይህ ምስል ትክክለኛ መልዕክት የያዘ ሳይሆን ያ መረጃ የሚያጠምደዉ ፕሮግራም ነዉ። ይህን ፕሮግራም አንዴ ኮምፕዩተርሽ ዉስጥ ከገባ ወደማዘዣዉ ኮምፕዩተር መረጃዎችን በሙሉ እየቀዳ ይልካል። ይህ ነገር ኮፕዩተርሽ ዉስጥ ካለ እያንዳንዷ የምትፅፊያት ነገር ፕሮግራሙን ወደላከዉ አካል ይሸጋገራል።» እሳቸዉ እንደሚሉትም ሲቲዚን ላብ ባደረገዉ ክትትል የግለሰቦችን መረጃ እየቀዳ የሚልከዉ ህገወጥ ፕሮግራም ትዕዛዝ አስተላላፊ የኮምፕዩተር መረጃ ማከማቻ የሚገኘዉ እዚያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሆኑን ደርሶበታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በኢንተርኔት ላይ የሚከናወነዉን ጥብቅ ቁጥጥር እና ስለላ አስመልክቶችም ሲቲዚን ላብ ይፋ ያደረገዉን አዲስ መረጃ በማካተት ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዘገባ ይፋ እንደሚያደርግም ከወዲሁ ጠቁመዋል።

ምንጭ፥    http://www.dw.de/%E1%8D%8A%E1%8A%95-   %E1%8D%8A%E1%88%B8%E1%88%AD-%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%8B%A9-%E1%89%AB%E1%8B%AD%E1%88%A8%E1%88%B5/a-16678127