1
Posted December 1, 2012 in Amharic news
 
 

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ!


ከሰሞኑ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ቁጥጥር ሥር ያለችው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባል ሆና ተመርጣለች። በዚህ አህጉራዊ ኮታን አንጂ የአገሮችን ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሬኮርድ እንደ መመዘኛ በማይወስደዉ ምርጫ ከአፍሪካ አህጉር ኢትዮጵያን ጨምሮ ኩትዲቯር፤ጋቦን፤ኬንያና ሴራሊዮን የጉባኤዉ አባል ሆነዉ ተመርጠዋል። በሰብአዊ መብት ረጋጭነቷ የምትታወቀዉ ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባል ሆና የመመረጧ ዜና እንደተሰማ በህወሀትና በደጋፊዎቹ መንደር ሠርግና ምላሽ ሆኖ ሰንብቷል።

የህወሀት ባለስልጣኖቸችና በአለም ዙሪያ የሚገኙ ጀሌዎቻቸዉ ከሰሞኑ እስክስታ ቀረሽ ዘፈን መዝፈን የጀመሩት ኢትዮጵያ ለመንግስታቱ ጉባኤ የተመረጠችዉ የአገሪቱ የስብአዊ መብት ጥበቃ በመልካም ደረጃ ላይ ስለሆነ ነዉ ብለዉ ስለምያምኑ ነዉ። ወንጀላቸዉና በህዝብ ላይ የሚፈጽሙት ግፍና በደል የማይታያቸዉን የህወሀት ባለስልጣኖች ከብዙዎቻችን ልዩ የሚያደርጋቸዉ ባህሪይ ቢኖር ዉሸትን እዉነት ነዉ ብለዉ ስለሚያምኑ ነዉ። ይሄ ደግሞ በሽታ እንጂ ጤንነት አይደለም። አንደ ጵላጦስ እጅን በዉሀ ታጥቦ ከደሙ ንጹህ መሆን አይቻልም።

እዚህ ላይ በአንድ በኩል የሚያስገርሙ በሌላ በኩል ደግሞ የሚያሳዝኑ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛዉ  ኢትዮጵያ የተመድ የስብአዊ መብቶች ጉባኤ ኣባል ሆና የተመረጠችዉ የወያኔ ዘረኞች ደራ ወረዳ ዉስጥ አገርን ጉድ ያሰኘና የሰው ልጆችን ክብር ያዋረደ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በፈጸሙ ማግስት መሆኑ ሲሆን ሁለተኛዉና አሳዛኙ ነገር ደግሞ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በሰዉ ልጆች መብት ረገጭነቷ ቤመድረኩ ላይ ስሟ የሚነሳዉን ኢትዮጵያን ለዚህ በየአገሩ የሚታየዉን የሰዉ ልጅ መብት ጥሰት ለሚከታተለዉ ከፍተኛ አካል አባል አድርጎ መምረጡ ነዉ። ከዚህ ቀደም ኢራንንና ኢራቅን የመሳሰሉ መብት ረጋጭ አገሮች አባል አድርጎ የመረጠዉ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በረጂም አመት ታሪኩ ይህ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ስራ ሊሰራ ያልቻለዉ ኢትዮጵያን፤ ኢራንንና ጋቦንን የመሳሰሉ የለየላቸዉ መብት ረጋጭ አገሮች አባል አድርጎ ሰልሚመርጥ ነዉ።

የህወሀቷ  ኢትዮጵያ የምትታወቀው የሰው ልጆችን መብት በመርገጥ እንጂ በማክበር አይደለም። ፖለቲከኞችን፤ ጋዜጠኞችን፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በማሰርና በማንገላታት ከሚታወቁ አገሮች መካከል ግንባር ቀደሟ የወያኔዋኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ዉስጥ የወያኔን አገዛዝ ተቃውመዋል የተባሉ ዜጎች አሸባሪ ተብለው መታሠር ብቻ ሳይሆን ብልቶቻቸውን ተቀጥቅጠው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። አጥበተው ያሳደጉ እናቶች ጡቶች በሽቦ እንዲገረፍ ተደርጓል። በሽብርተኝነት ተከስሰዉ የሚታሰሩ ዜጎች ንብረት ተወርሶ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ለእርዛትና ለድንቁርና ተዳርገዋል። እንግዲህ ይህች ኢትዮጵያ ነች በሰብዓዊ መብት ካውንስል ውስጥ አባል ሁና እንድትቀመጥ የተደረገው።

ኢትዮጵያ የመንግስታቱ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባል ሆና የተመረጠችዉ ማንም አገር እንደሚመረጠዉ አህጉራዊ ኮታ ለሟሟላት መሆኑ በግልጽ እየታወቀ ሕወሃቶች ግን የተመረጥነው ኢኮኖሚያችን አድጎ ዜጎች በቀን ሦስት ግዜ በልተው ማደር በመቻላቸው፤ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመቻሉና ፍትሃዊ ምርጫ ተደርጎ ህዝቡ የመረጠው 99.6% አካል ስልጣኑን መያዝ በመቻሉ፤ዜጎች የልባቸውን ለመናገር ከፍርሃት መውጣት በመቻላቸው ነው እያሉ የገዛ ውሸታቸውን አምነዋል።ዜጎችም የወሮበላዎችን ውሸት እውነት ነው ብለው እንዲያምኑላቸው ደፋ ቀና እያሉ ነው።የገዛ ውሸትን እውነት ብሎ ማመን በሽታ ነው።ህወሃት ደግሞ በዚህ በሽታ የሚሰቃይ ድርጅት ነው።

በአንድ ወቅት በአሜሪካን መንግስት ሰነድ ውስጥ አሸባሪ ተብሎ የተመዘገበው ሕወሃት ከኖረበት ፅልመት ወጥቶ የሰው ልጆችን መብት የሚያከብር ቡድን ይሆናል ብሎ ማመን ለሌሎች ይቅርና ለራሱ ለሕወሃት የሚቻል አይደለም። ህወሃት በተፈጥሮው አሸባሪ ነው።ይህን ተፈጥሮውን መቀየር የሚችል ቡድንም አይደለም። ሕወሃት ከኖረበት ፅልመት ውስጥ ወጥቶ ብርሃን ወዳለበት እንዲመጣ የቆመበትን መሠረት ዞር ብሎ ማየት መቻል ይኖርበታል።ይህ ደግሞ ለግትሮቹ ህወሃቶች የሚቻል አይደለም።የእነርሱ አንገት የተሠራው አዙሮ ለማየት ሳይሆን ያን በብቀላና በጭካኔ የተሞላውን ጭንቅላት ለመሸከም ብቻ ነው።

የተከበራችሁ የአገራችን ዜጎች የሚረዳን ማንም የለም።ክብራችንና ነፃነታችንን የምናስመልሰው እኛው ብቻ ቆርጠን በመታገል ነው።ነፃነታችንን ከዚህ ወይም ከወዲያ ማዶ መጥቶ የሚሰጠን ማንም የለም።ነፃነታችን በእጃችን ነች።ሞት ወይም ነፃነት ማለት ካልቻልን ነፃነት እንዲሁ በደጅ ጥናት የምትገኝ አይደለችም።

በመጨረሻም ይህን ፅልመት የወረረውን የወሮበላ ቡድን ከአገራችን ጫንቃ ላይ አውርደን ወዲያ በመጣል የአገራችንን መልካም ዝና መትከል የኢትዮጵያዊያን ድርሻ ነው።ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ከኢትዮጵያዊያን ውጪ ሌላ ኃይል ከየትም አይመጣምና በየአቅጣጫው የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!