1
Posted November 29, 2012 in Amharic news
 
 

“ሕዝቡ ከማጉረምረም አልፎ ንዴቱን በእንቅስቃሴ ለማሳየት ዝግጁ የሆነ አይመስልም” – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ


ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር

(REPORTER) – ባለፈው እሑድ ኅዳር 16 ቀን 2005 ዓ.ም. አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባደረገው ውይይት ላይ የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶተኛና በማጉረምረም ደረጃ ላይ የሚገኝ እንጂ፣ ንዴቱን በእንቅስቃሴ ለማሳየት ዝግጁ የሆነበት ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስልም አሉ፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በዳሰሱበት ክፍል ላይ በሰጡት ማብራሪያ ሕዝቡ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸው፣ ይህንን ሰቆቃውንና ብሶቱን ያማርራል እንጂ በይፋና በአደባባይ አይገልጽም ብለዋል፡፡ “ብሶቱ በማጉረምረም ደረጃ የሚገለጽ ነው እንጂ ወደ ኅብረተሰባዊ ንዴት አልተለወጠም ብለው፣” የተናጠል ንዴቶች አልፎ አልፎ ቢገለጹም ሰፊና የአጠቃላይ ኅብረተሰቡ አለመሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

“እነዚህ የተናጠል ትናንሽ ንዴቶች ወደተደራጀና ሕዝባዊ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች አልተለወጡም፡፡ በሌሎች አገሮች በዳቦ ወይም በነዳጅ ዋጋ ላይ ትንሽ ጭማሪ ከታየ የኅብረተሰቡ ንዴት ይገነፍላል፡፡ በእኛ ሕዝብ ዘንድ ግን ይህ አይታይም፡፡ ምልክቶች ከታዩ ጥቂት፣ የተናጠል፣ ያልተደራጁና ያልተቀናጁ ናቸው፤” ብለዋል፡፡

ዶክተር ነጋሶ ገዥው ፓርቲ አምባገነን መሆኑን ባሰፈሩበት ክፍል፣ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ደንታ የሌለው ድርጅት መሆኑን ገልጸው፣ የሕዝብን ፍላጎት አያዳምጥም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ “ሕዝብ እሱን ብቻ መስሎ እንዲያድር ነው የሚፈልገው፡፡ ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ ፓርቲውን ያስቀድማል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትንና በአንቀጽ 29፣ 30፣ 31 እና 38 የተዘረዘሩትን መብቶች አፍኗል፤” ካሉ በኋላ፣ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት ብሎ ሕጎችን በማውጣት ሕግ አስከብራለሁ በማለት ሰብዓዊ መብቶችን እንደሚጥስ አስታውቀዋል፡፡

ኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት እንዳይኖሩ አድርጎአል ብለው ሦስቱ የመንግሥት አካላት የሕዝብ አገልጋዮች ሳይሆኑ የፓርቲው መሣርያ ሆነዋል ብለዋል፡፡ “ገዥው ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን አያከብርም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተከበሩ መብቶች ተግባራዊ ይሁኑ ሲባል አይፈቅድም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን መንገድ ከመክፈት ይልቅ በሚያወጣቸው ሕጎች በእጅ አዙር ያሻሽላል፡፡ በአሠራሩ ሕገ መንግሥታዊ አስተሳሰብን ዋጋ አሳጥቷል፤” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን በገለጹበት ክፍል ደግሞ የፓርቲ ሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑን አውስተው፣ በሕገ መንግሥቱ ቢደነገግም ዲሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በኢትዮጵያ የለም ብለዋል፡፡ በንጉሡ ዘመን በፓርቲ መደራጀት ክልክል መሆኑን፣ በደርግ የመጀመሪያ ዓመታት ለደርግ ታማኝ የሆኑ ለስሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢወለዱም በመጨረሻ አገሪቱ በአንድ ብቸኛ ፓርቲ (ኢሠፓ) ሥር መውደቋን፣ ኢሕአዴግ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይመሠርታል ተብሎ ቢጠበቅም የአውራ ፓርቲ ሥርዓት መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡

“ይህም አውራ ፓርቲነት እንደ አሜሪካና እንደ ታላቋ ብሪታኒያ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ የሁለት ፓርቲዎች አውራነት ቢሆን ባልገረመን፣ ወይም እንደ ጃፓንና እንደ እስራኤል ዴሞክራሲያዊና መድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሰፈነበት አውራ ሆኖ ቢመጣ እንቀበል ነበር፡፡ እርሱ ግን በአስገዳጅነት አንድ አውራ ፓርቲ ሆኖ ሌሎች ግን እንደ ጫጩት እንኳ እንዳይኖሩ በሙስና አሠራርና በልዩ ልዩ ተፅዕኖ ሥር ለማዳ ያደርጋቸዋል ብሎም ከነጭራሹ እንዲጠፉ ያደርጋል፤” ብለዋል፡፡

የምርጫ ሥርዓቱን ብልሹ ነው ያሉት ዶክተር ነጋሶ፣ የምርጫ ሥርዓቱ ለአገሪቱ ውስብስብ ሁኔታዎች ምቹ አለመሆኑን፣ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ብዙ ሃይማኖቶችና የተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ባሉበት አገር አሸናፊው ሁሉንም የሚወስድበት ሥርዓት እንደማይች አስረድተዋል፡፡ “ማኅበረሰባዊ ውክልና፣ ተጠያቂነትና የአሳታፊነት መርህን የተከተለ የተመጣጠነ ሥርዓት እንዲኖር አይፈለግም፡፡ ይባስ ብሎ በምርጫዎች መካከልና በምርጫዎች ወቅት ያለው የፖለቲካ ምኅዳር የተስተካከለ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነፃነት የተሟላበት አይደለም፡፡ በዚህ የምርጫ ሥርዓት ውስጥ ተሸናፊ ፓርቲዎችን የሚመርጥ ብዙ ሚሊዮን የሕዝብ ክፍል በፓርላማ ደረጃ ድምፅ አልባ ይሆናል፤” ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ነጋሶ የፖለቲካ ልዩነቶችና ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ሳይሆን በጉልበት መሆኑን፣ የሕዝብ ወሳኝነት እንደማይፈለግ፣ ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ሲባል ሰፊና አገራዊ የትብብር መድረክ ለመፍጠር ፈቃደኝነትና ዝግጁነቱ ደካማ መሆኑን ጠቅሰው፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተለመደው በአሸናፊነት የማንበርከክ ፍላጎትና የበላይነት ማስፈን አካሄድ በመሆኑ እምቢ ከተባለ ደግሞ ለማጥፋት መንቀሳቀስ መኖሩን አውስተዋል፡፡ ሰላማዊ የትግል ስልቶችን መጠቀም አለመጀመሩን ገልጸው ሰላማዊ ትግል ኃይል አልባ፣ ሕጋዊ፣ ሕገ መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ፣ አንዳንድ ሕጎችና ተቋማት የሌሎችን መብቶች የሚነኩ ከሆነ እምቢ ማለትና ያለመታዘዝን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡ “ሰላማዊ ትግል የተቃውሞ መሣርያ እንጂ የአመፅ መሣርያ አይደለም፤” ብለው፣ ሰላማዊ ትግል ሰፊ የመደራጀትና የዝግጅት ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የወደፊት የትግል አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት ሲገልጹ፣ ሕዝብን ለለውጥ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራትና በሕዝብ ውስጥ የማደራጀትና የማቀናጀት ሥራዎች መሠራት አለባቸው ብለዋል፡፡ ገዥውን ፓርቲ ለለውጥ በማስገደድ ሰፊ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ብልሹ ያሉትን የፓርቲ ሥርዓት በመለወጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲስተካከል በቁርጠኝነት ትግል መደረግ አለበት ሲሉ አመልክተዋል፡፡

“በአገራችን ለችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ እርቅ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶችን ወይም ችግሮችን ለመፍታት አንድነት በፕሮግራሙ ያስቀመጠው አቅጣጫ ትክክል ነው፡፡ ስለሆነም ችግሮችን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ በውይይትና በድርድር የመፍታትን ባህል የበለጠ ማዳበር የትግላችን አቅጣጫ መሆን አለበት፤” በማለትና አንዳንድ ነጥቦችን በማከል ዳሰሳቸውን ደምድመዋል፡፡

http://www.ethiopianreporter.com/news/2 … eview=true