0
Posted November 28, 2012 in Amharic news
 
 

“የኢትዮጵያ ዘመናዊ የህፃናት የውጭ ንግድ“


ሔለን ዘውዱ አየለ  ከኖርዌይ

በአንድ ህፃን ከ20ሺ ዶላር በላይ

የጉዲፈቻ ታሪክ በኢትዮጵያ በባህላዊ መንገድ ሲደረግ የቆየ ነው መቼ እንደተጀመረ በእርግጠኝነት ለማወቅ ባይቻልም በ18 ክፍለ ዘመን በኦሮሞ ብሔረሰብ እንደተጀመረ ይታሰባል። ጉዲፈቻ የሚለው ቃል የመጣው ከኦሮሚኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጓሜውም ተፈጥሮዓዊ የወላጅነትና የልጅነት የሥጋ ዝምድና ሳይኖር ከሌላ ሰው አብራክ የተወለደን ልጅ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ጥቅሙን ጠብቆ እንደ አብራክ ክፋይ ልጅ ማሳደግ ማለት ነው። በኢትዮጵያ የጉዲፈቻ ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ማዕቀፍ ተሰጥቶታል ይህም ሕግ የሕፃኑን መብት የሚያስጠብቅ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።

የጉዲፈቻ ዓላማ ከውርስ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የዘር ሃረግን ለመቀጠል፤ የዝምድና ትስስር ለማጠናከር፤ ፖለቲካዊ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማግኝት፤ … ጥቂቶቹ ናቸው። ለምሳሌ በሀገራችንም የተለያዩ ጦርነቶች በጎሳዎች መካከል ሲነሱ የአንዱን ጎሳ ልጅ አንዱ ጉዲፈቻ ያደርጋል በዚህም ሰበብ በጎሳዎቹ መካከል ሰላም ይፈጠራል።

በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት የድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ እየጨመረ መጥቷል። ሀገሮች ለጉዲፈቻ ልጆች ምንጮች የሚሆኑበት ምክንያት በርካታ ናቸው። በሃገራችን እ. ኤ. አ. በ2004 በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ከቻይና፣ ጓቲማላ፣ ሩሲያና ሶሪያ ቀጥላ በአምስተኛ ደረጃ የጉዲፈቻ ምንጭ ሀገር ለመሆን መብቃቷ ታውቋል። እ. ኤ. አ. በ2006 ላይ የተለያዩ ሀገሮች እየቀነሱ በመምጣታቸው ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እ. ኤ. አ. በ2010 ደግሞ አብዛኞቹ ሃገሮች በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሳቸው ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሆናለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ የጉዲፈቻ መስፋፋት ምክንያት የጉዲፈቻ ኤጀንሲ ማቋቋም ቀላል በመሆኑ ነው።መንግስት ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችለው አሰራር እንደሌለው እና ድርጅቶቹን በቀላሉ አቋቁሞ በአንድ ህፃን ከ20ሺ ዶላር በላይ እየተቀበሉ ሕፃናትን ከሃገር ማጋዛቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ጉዳይ አስፈጻሚ (Case worker) ተብለው በሚጠሩ ቅጥረኛ ሕፃናት መልማዮች እና ከሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች ከጉዲፈቻ ኤጀንሲዎች ጋር በመመሳጠር ሕፃናትን በመስረቅ ለተለያዩ የውጭና የሃገር ውስጥ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች የሚሸጡ እንዳሉ በስፋት ይነገራል።

የልጆቹ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ ደህንነት፣ የወላጆች ሁኔታ ከግምት ባልገባበት የጉዲፈቻ ሂደት ሕፃናትን ከሃገር በማስውጣት ረገድ በተለይ ህጻናትን የሚያሳድጉና ለውጭ ሃገር በማደጐነት የሚያስተላልፉ ድርጅቶች፣ ሕፃናቱን ከየትና በምን ሁኔታ እንዳገኟቸው ቁጥጥር ስለሌለ ህገወጥ ንግዱ ተስፋፍቷል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በዓለም የጉዲፈቻ ተመራጭ መድረሻም መሆኗ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የሚዘገበው። ከጉዲፈቻ ጋር በተየያዘ በመንግስትና በጉዲፈቻ ድርጅቶች በኩል ያሉ የፖሊሲዎችና የአፈፃፀም ክፍተቶች በመኖራቸው አሠራሩ “የኢትዮጵያ ዘመናዊ የህጻናት የውጭ ንግድ” የሚል ስም ተሰጥቶታል። ይህንን የመንግስት ቅሌት Nov. 19 2012 አምስተርዳም በተከፈተው አለም አቀፍ የዶክመንታሪ ፊልም ፌስቲቫል ላይ Mercy Mercy የተሰኝው ፊልም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራውን ህግ ወጥ የህፃናት ንግድ አጋልጦዋል። እየተካሄደ ያለው ልቅ አሠራር የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሳይቀር በሃገራችን የጉዲፈቻ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችን በመክፈት እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል።

ሕፃናትን የሚመለከቱ ውሳኔዎች በሚሰጡበት ጊዜ በሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት የሕፃናት ጥቅምና ደህንነት ከማናቸውም ቅድሚያ እንደሚሰጠው፤ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ለሕፃናቱ ደህንነት ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት የሕፃናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ እንዳለበትም ይደነግጋሉ፡፡

በብዙ ሃገሮች ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ብዙዎችንም የሚያስማማው የጉዲፈቻ ዝምድና ዓይነት “በግልጽ የሚደረግ የጉዲፈቻ ልጅነት” (Open Adoption) የምንለው ነው፡፡ የልጁ ወይም የልጅቷ ተፈጥሮዓዊ ወላጆች የልጃቸውን የጉዲፈቻ ወላጅ በመምረጥና በመለየት በጉዲፈቻ ከተሰጠው ልጃቸው ጋር ያለው የወላጅነት ዝምድና ሳይቋረጥ እንደቀጠለ የሚቆይ የጉዲፈቻ ዝምድና ዓይነት ነው፡፡ ሌላውና በብዙ አገሮችም ሆነ በብዙ ሰዎች ተቀባይነት የሌለው የጉዲፈቻ ዓይነት “በግልጽ ያልተደረገ የጉዲፈቻ ልጅነት ማለት” (Closed Adoption) ተፈጥሮዓዊ የሆኑ ወላጆች ራሳቸውን በመደበቅ ወይም ወላጅነታቸውን በመሰወር የጉዲፈቻ አድራጊ ለሆነው ሰው (አሳዳሪ) በጉዲፈቻ የተሰጠውን ልጅ በመልቀቅ የወላጅነት መብታቸውን የሚያጡበት ነው፡፡

ከእነዚህ ሁለት የጉዲፈቻ የዝምድና ዓይነቶች አገራችን የመጀመሪያውን ማለትም “በግልጽ የሚደረግ የጉዲፈቻ የዝምድናን” ዓይነት እንደመረጠች ከቤተሰብ ሕጉ የተለያዩ ድንጋጌዎች እንረዳለን፡፡ በወረቀት ላይ የሠፈረው አካሄድ ይህን የሚመስል ቢሆንም በሃገራችን የሚደረገው የጉዲፈቻ ሂደት የጉዲፈቻ አድራጊውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በመረጃ ደረጃ ከሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት ጋር ተመሳጥረው ልጆቹ ሲላኩም ምንም ዓይነት የመገናኛ ዘዴ እንዳይኖር ተደርጎ የሚላኩበት ሁኔታም አለ፡፡ በአብዛኛው ጉዲፈቻ አድራጊ ወላጆቻቸው እያሉ የሞቱ መሆኑን እያስመሰከሩ የሚልኩና ጥቅም እንደሚያገኙ ነው፡፡

 መንግሥት የመጨረሻ አማራጫቸው ይሄ ነው ብሎ ከሌላ ሀገር ለመጣ ዜጋ በማሳደጊያ ያሉትን ልጆች በሕጋዊ መንገድ ወስዶ የሚያሳድግበት አካሄድ ነው። ሕፃናቱ በሄዱበት አገር ተመችቷቸዋል ወይስ አልተመቻቸውም የሚለውንና የማንነት ችግር እንዳያጋጥማቸው መንግስት መከታተል ሲገባው ህጻናቱ ለአሳዛኝ ድርጊቶች እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ በተሰጣቸው የተሳሳተ መረጃ በግልፅ ባልተረዱት አሠራር ልጆቻቸውን በጉዲፈቻ ሰጥተው ስለ ልጆቻቸው አንዳችም ነገር ማወቅ ያቃታቸው ኢትዮጵያውያን ወላጆች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ በጨቅላነታቸው ወደ ውጭ ሄደው ከማንነት ጥያቄ ባሻገር ለከባድ ሥነልቦናዊና አካላዊ ጉዳት የተጋለጡ ልጆች ቁጥርም ጥቂት አይደለም፡፡ በፈረንሣውያን ባልና ሚስት የሁለት ዓመትና የአራት ዓመት ወንድ ልጆች ሊያሳድጉ ከኢትዮጵያ በወሰዱ ማግስት ነበር በአሳዳጊያቸው የተደፈሩት፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ሀና ዊልያምስን አሜሪካ ውስጥ በምግብ እጥረት ሕይወቷ አልፏል፡፡ አምስት ኢትዮጵያዊያን ሴት ልጆች በአሳዳጊያቸው የመደፈራቸው ዜና መዘገቡም ይታወሳል፡፡ የማንነት ቀውስ ለአንድ ሕፃን ልጅ የመጨረሻው መጥፎ ክስተት ነው።

 

መንግሥት ጉዲፈቻን እንደማያበረታታ ይናገራል፡፡ የሴቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ሚኒስቴር በጉዲፈቻ የሚሄዱ ሕፃናትን ጉዳይ በተመለከተ በቀን ከሀምሳ በላይ የሚሆኑ ማመልከቻዎችን እንደሚያስተናግድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሆኖም ምዕራባዊ የዜና አውታሮች በማስረጃ እንደሚዘግቡት በአሜሪካ በጉዲፈቻነት ልጅ ከሚደረጉ አምስት ህጻናት መካከል አንዱ ከኢትዮጵያ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በአሜሪካ ብቻ እ.ኤ.አ. በ2004 በጉዲፈቻነት ከኢትዮጵያ የሚመጡት ህጻናት ቁጥር በ2010ዓም በሦስት እጥፍ ያደገ ሲሆን ይህም አገራችንን ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛ አድርጓታል፡፡