0
Posted September 4, 2014 in News
 
 

ወጣቱን ለማደንቆር ያለመው ስልጠና ህወሓትን ለመቅበሪያነት ይዋል!


ህወሓት፣ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በየቦታው ሰብስቦ እያሰለጠነ ነው። ይህ ሲያልቅ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስልጠና ይቀጥላል ተብሏል። በድምሩ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ወጣት አንድ አይነት ሰነድ አንብቦ ለ2007 ትምህርት ይዘጋጃል ማለት ነው። ስልጠናው ወደ መንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ይስፋፋል ተብሎ ይገመታል።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በዚህ ሥልጠና ላይ ያለውን እይታ በነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓም ቁጥር 328 ርዕሰ አንቀጹ መግለጹ ይታወሳል። ግንቦት 7 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ስልጠናዎች ላይ ተቃውሞ ለማሰማት መድፈራቸው ወጣቱ ለለውጥ የተዘጋጀ እንደሆነ አመላካች መሆኑን ተገንዝቦ ይህ የለውጥ ፍላጎት በድርጅት እንዲታገዝ ወጣቱ በትናንሽ ሕዋሶች ራሱን እንዲያደራጅ መክሯል። ሆኖም ግን ህወሓት ለስልጠናው የሰጠው ትኩረት ቀድሞ ከታሰበው በላይ በመሆኑ ንቅናቄዓችን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደገና ሊመለስበት ወስኗል።

ህወሓት፣ ይህንን ያህል መጠነ ሰፊ ስልጠና ማድረግ ለምን አስፈለገው? የዲሞክራሲ ኃይሎችስ ይህንን ስልጠና እንዴት ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ?

ህወሓት ይህንን ትርጉም የለሽ ስልጠና በአሁኑ ሰዓት ለመስጠት የፈለገበትን በርካታ ምክንያቶች ማቅረብ ቢቻልም የሚከተሉት ሁለቱ ግን ዋነኛዎቹ ናቸው ብለን እናምናለን።

አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ህወሓት የተከታዮች ድርቅ የደረሰበት መሆኑ አድርባይ መሪዎቹን ማሳሰቡ ነው። በሚሊዮን ይቆጠራሉ የሚባሉት የኢህአዴግ አባላት ልባቸው ከህወሓት ጋር አለመሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በተለይ ደግሞ በተላላኪዎቹ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደህዴግ የተሰባሰቡ አባላት በግልጽ ህወሓትን መቃወም እየጀመሩ ነው። ህወሓት የራሱን መጥፊያ እያደራጀ መሆኑ የተሰማው በመሆኑ አዳዲስ “ምዕመናንን” ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ መመልመል ይፈልጋል። የመንግሥት ንብረትና መዋቅር ለፓርቲ ስልጠና የሚጠቀም በመሆኑ ከብዛት የሚገኝ ትንሽም ቢሆን ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ የወጭው ጉዳይ ህወሓትን አያሳስበውም። ስለሆነም ይህ ስልጠና በተቻለ መጠን ብዛት ያላቸዉን የተማተሩ ወጣቶች በአድርባይነት ለህወሓት ማሰለፍን አላማዉ አድርጎ የተነሳ ስልጠና ነዉ።

ሁለተኛው አቢይ ምክንያት ደግሞ ህወሓት ለኢትዮጵያ ወጣት ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ወደ እያንዳንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ጆሮ መድረሱን ማረጋገጥ መፈለጉ ነው። መልዕክቱም “ሜዳ ውስጥ ያለሁት ተጫዋች እኔ ብቻ ነኝ። ለሚቀጥሉት አርባና አምሳ ዓመታትም እኔን የሚገዳደረኝ አይኖርም፤ ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣት ሆይ ለለውጥ ያለህ ተስፋ ከንቱ ነው። አርፈህ ቁጭ ብለህ ተገዛ” የሚል መልክት ነው።

ስልጠናዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ዓላማዎችን በሚገባ ማስፈፀም ይችላሉ ብሎ መገመት ከባድ ነው። የስልጠናው ይዘት እጅግ የወረደ እና የሰልጣኞቹን ብስለት ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆኑ ስልጠናውን ምፀት የበዛበት አድርጎታል፤ አሰልጣኞቹንም ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል። የስልጠናዎቹ ጽሁፎች (ማንዋሎች) ይዘት ደግሞ የአዘጋጆቹ የእውቀት ማነስ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑ ለተማሪዎቹ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሆነውላቸዋል። በአጠቃላይ ስልጠናው ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ያልተዘጋጁበት ፈተና ደቅኖባቸዋል። የኢትዮጵያ ወጣት ሲሞሉት የሚሞላ ባዶ ጋን አለመሆኑን እያዩት ነው። ወጣቶች ጠጣር ጥያቄዎችን ያነሱባቸዋል፤ አሰልጣኖች እነዚህ ጥያቄዎች እንዴት መመለስ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ይደናበራሉ። መልስ ሲጠፋ ቁጣ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ይከተላል።

ይህም ሆኖ እነዚህ ስልጠናዎች ለህወሓት ምንም ውጤት አያስገኙም ብሎ ማለፍ አይቻልም። የስልጠናዎቹ ውጤት የሚወሰነው ግን የኢትዮጵያ ወጣት ከህወሓት ውጭ ለሚመጣ መረጃ ባለው ቅርበት መጠን ነው። ሁሉም የመረጃ ምንጮች ተዘግተውበት የህወሓትን የእድገትና የሰላም መዝሙር ሲሰማ ለኖረ ሰው በስልጠናው የሚሰጡ ባዶ ፕሮፖጋንዳዎችን የመቃወሚያ ምክንያት አይኖረውም። ለተለያዩ የመረጃ ምንጮች ቅርበት ያለው ወጣት ግን የህወሓት መዝሙር ከግራዚያኒ የእድገትና የሰላም መዝሙር የተለየ አለመሆኑን ይረዳል። በፋሺስት ወረራ ወቅት ግራዚያኒም ኢትዮጵያን በመንገድና በህንፃ እየገነባሁ ነው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አውሮፓ የደረሰችበት ደረጃ ላይ አደርሳታለሁ ይል እንደነበር ይታወሳል።

የህወሓትን ኢትዮጵያን ለአርባና አምሳ ዓመታት የመግዛት እቅድን ወጣቱ ምክንያታዊ ነው ብሎ ይቀበላል? የራሱን አፋኝ ህጎች አክብረው እየተፍጨረጨሩ ያሉ ተቀናቃኖቹን እንኳን በእንጭጩ እየደፈጠጠ ያለ ሥርዓት “ኃላፊነት የሚሸከም አጣሁ” የሚለው ሰበቡ በወጣቱ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል? በግንቦት 7 እምነት ይኸኛው የስልጠና ዓላማ ሊሳካ የሚችለው በዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ድክመት ብቻ ነው። ዘረኛውንና ዘራፊውን ወያኔ መጣል ብቻ ሳይሆን ከወያኔ በኋላ ፍትህ፣ እኩልነትና ብልጽግና የሚሰፍኑበትን ስትራቴጄ ያዘጋጀና ለስትራቴጂዉ ክንዉንራሱን ያዘጋጀ ድርጅት መኖሩን የኢትዮጵያ ወጣት ማወቅ ይኖርበታል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሌሎች ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ወደ ነፃነት፣ እኩልነትና ብልጽግና ጎዳና ለማስገባት እየታገለ መሆኑን ሁሉም ወጣት ሊገነዘብ ይገባል። ይህ ግንዛቤ ካለ የኢትዮጵያ ወጣት ለእብርተኛው፣ ዘረኛው፣ ሙሰኛውና ከፋፋዩ ህወሓት ተገዢ አይሆንም።

በስልት ከተጠቀምንበት ህወሓት ብዙ ሚሊዮኖች የሕዝብ ገንዘብ አውጥቶበት ያዘጋጀው ስልጠና ለራሱ ከሚሰጠው ጥቅም በላይ ለዲሞክራሲያዊ ኃይሎች የሚሰጠው ጠቀሜታ ይበልጣል። ለምሳሌ፣ ግንቦት 7 እነዚህን ስልጠናዎች የኢትዮጵያን ወጣት ለትግል ያላቸውን ዝግጁነት ለመገምገም ተጠቅሞበታል። “የኢትዮጵያ ወጣት ለትግል ዝግጁ ነው – የቀረው ድርጅት ነው” ሲል የግምገማውን ውጤት አሳውቋል። በዚህም ርዕሰ አንቀጽ ይህንኑ መልዕክት ማስረጽ ይፈልጋል።

በአምባገነን ሥርዓቶች ውስጥ የሚኖሩ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች ከተለመዱ አደረጃጀቾች መለየት አለባቸው። መደበኛ (Formal) አደረጃጀቶች አባላትን ለአደጋ ያጋልጣሉ። በዚህም ምክንያት ነው ግንቦት 7፣ ኢ-መደበኛ (Non Formal) አደረጃጀቶች የሚመርጠው። በእኛ ሁኔታ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” ስንል አራት ይሁን አምስት የሚተማመኑ ወጣቶች የሚፈጥሩት የግንቦት 7 ሴል ነው። ይህንን ሴል የፈለጉትን ስም ሊሰጡት ይችላሉ – እድር፣ ክበብ፣ የሆነ ስፓርት ቡድን ደጋፊ የተመቻቸውን ስያሜ ይስጡት። የተቋቋመበት ዓላማ ግን ግልጽ ነው – ለፍትህና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ማገዝ ነው። ይህ ኢ-መደበኛ ስብስብ ራሱን የግንቦት 7 አካል አድርጎ ይቁጠር። የግንቦት 7 ፕሮግራሞችንና ጽሁፎችን ያንብብ። ስብስቡ ለመረጃዎች ራሱን ቅርብ ያድርግ። መረጃዎችን ይለዋወጥ። በሂደት ቀጣዩ መንገድ ግልጽ እየሆነለት ይመጣል።

እየተካሄደ ያለው የህወሓት የጅምላ ስልጠና ለኢ-መደበኛ ድርጅቶች መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች እነዚህን ስልጠናዎች የግንቦት 7 ሴሎችን ለማደራጀት እንዲጠቀሙበት እንመክራለን። ግንቦት 7 በኢትዮጵያ ወጣት የፈጠራ ችሎታ ላይ እምነት አለው። የኢትዮጵያ ወጣት አደንቁሮ ሊቀብረው የመጣውን ስልጠና ህወሓትን ለመቅበሪያነት እንደሚጠቀምበት የግንቦት 7 እምነት ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!