0
Posted December 17, 2013 in News
 
 

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የተመሰረተበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ


ታህሳስ 7  2006 ዓም የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ከተመሰረተ  አንድ አመት ሞላው። አንድ አመት  በጭንቅና  በአሳር  ለተያዘች የዛሬይቱ ኢትዮጵያና ህዝቧ እጅግ ረጅም ግዜ እንደሆነ ህዝባዊ ሃይሉ በሚገባ  ይገነዘባል። ባላፈው አንድ አመት ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የመከራ የአሳርና የውርደት ህይወት ይበልጥ እየሰፋ፣ የሚፈጸምበት ግፍ ይበልጥ እየገዘፈ መሄዱን አይተነዋል። በሃገርና በህዝብ ላይ እየወረደ ያለውን ወያኔ ወለድ የስቃይና የፍዳ ናዳ በቅጡ ላጤነው  ሃገሪቱና ህዝቧ የአዳዲስ የስቆቃና የመከራ አይነቶች መፈተኛ ቤተ ሙከራዎች እየተደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር አይኖረውም። ለሚራበው ለሚረገጠው በግፍ ለታጎረው፣ በኑሮ ውድነት ለሚጠበሰው፣ ለተሰደደው ለተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ እንድ አመት በሲኦል የቀናትና የወራት መቁጠሪያ እንደሚለካ ዘመን እጅግ የረዘመ የስቃይ ግዜ ነው።

Ginbot 7 Popular Force logo

የዋልድባ መነኩሳት ገዳማችን  አትድፈሩ አታፍረሱ በማለታቸው እየተገረፉ ለዘመናት ፈጣሪያቸውን ከሚማጸኑበት ለሃገርና  ለህዝብ ምልጃ ከቆሙበት ገዳም በዘር መመዘኛ እየተለዩ  እንደቆ ሻሻ ተጠርገው የተባረሩበት ፣ እምነታችን አትንኩ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችና  መሪዎቻቸው በሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው  ወህኒ መውረዳቸው አንሶ  ወንድሞቻችን ይፈቱ በማለት  ሰላማዊ  ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖቻቸን በወያኔ ነፍሰ- ገዳዮች  በአረመኔያዊ ጭካኔ የተጨፈጨፉት በዚሁ አመት ነው። ወያኔ በህዝብ መሃከል በዘራው የዘር መርዝ የተነሳ በሽዎች የሚቆጠሩ አማሮች ከጉራ ፈርዳና ከቤንሻንጉል፣ ኦሮሞዎች ለዘመናት ከኖሩበት ምስራቅ ሃረርጌ  አካባቢ  እንዲፈናቀሉና በገዛ ሃገራቸው መድረሻ ቢሶች  እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ አንድ አመት ውስጥ ነው። ጋምቤላዎች ሙርሲዎች አፋሮችና ሌሎችም ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች የተጨፈጨፉበት፣በልማት ስም ለመጡ የውጭ ወራሪዎችና ወያኔ ለፈጠራቸው ቱጃሮች ቦታ እንዲለቁ ተደርጎ ቀደምቶቻቸው ለዘመናት ከኖሩባቸው ቀየዎች እንዲነቀሉ ተደርገው እንደ አልባሌ ነገር የትም እንዲበተኑ የማድረጉ ሂደት ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ የቀጠለው በዚሁ አመት ነው። በዚሁ አንድ አመት በወያኔ የሃገሪቱ ገዥዎች በህዝብ ላይ የተፈጸመው  ጭካኔና ወንጀል ተዘርዝሮ  የሚያልቅ አይደለም።

ይህ ወያኔ  ሰራሽ ሃገር በቀል የውርደትና  የስቃይ ህይወት አልበቃ  ብሎ ወያኔ ከሳውዲ የጨለማ ዘመን ገዥዎች ጋር በመተባበር ወንድሞቻችን በሳውዲ አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዲታረዱ እህቶቻችን በቡድን በተደራጁ የሳውዲ ጎረምሳዎች  እንዲደፈሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ  ለኢትዮጵያውያን ያለውን እጅግ የከረረ ጥላቻ በአደባባይ ያሳየበት አመት ነው። እንዲህ አይነቱ የጅምላ ግፍና  ውርደት ከመከሰቱ በፊት ህዝባዊ ሃይሉ በአረብ ሃገር በባርነትና  በስደት የሚገኙ እህትቶቻችንን ወንድሞችችን ስቃይ  ስቃዩ አድርጎ በመውሰድ “ላንቺ ነው” በሚለው ድርጅታዊ መዝሙሩ “በባለጌ  አረቦች መዳፍ ውድ ክብራቸው ለጎደፈው እህቶቻችን፣ በአረቦች የባርነት ቀንበር ጀርባቸው ለጎበጠው  ወገኖቻችን እንደርስላችኋለን፣ የተሰባሰብነው  ደማችን የሚፈሰው የመከራ ቀናችሁን ለማሳጠር ነው” የሚል ቃል ኪዳኑ ሰጥቶ  ነበር። የድርጅታችንን ምስረታ አንደኛ  አመት ስናከብር ልባችንን ደስታ ሳይሆን ሃዘን እንዲሞላ የሚያደርገው ይህ ቃል ኪዳናችን ለማክበር የጀመርነው ጉዞ ከድርጅት ምስረታና ከድርጅታዊ ዝግጅት አልፎ   በኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና ንቀት  የተነፋውን የወያኔን እብሪት በማስተንፈስ የወሰዳቸው ተጨባጭ የአለኝታነት እርምጃዎች ባለመኖራቸው ነው።

ምንም እንኳን ግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል እራሱን እንደ ድርጅት አቁሞ  ኢትዮጵያውያንን አሰባስቦ  መራራው ትግል የሚጠይቀውን የፖለቲካ  የወታደራዊ ስልጠናና ትጥቅ አስታጥቆ  በወያኔ  ላይ ለመዝመት የጀመረውን ጉዞ የሚያስቆመው ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ብናውቅም የህዝብ ስቃይ ለግዜው መቀጠሉ የህባዊ ሃይሉን አባላት ማሰቃየቱ አልቀረም። በወያኔ  ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው ወገናችን ህዝባዊ ሃይሉ የወያኔን አገዛዝ እድሜ  የሚያሳጥሩ ፈጣን እርምጃዎችን እንዲወስድ በከፍተኛ  ጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ  እናውቃለን። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች በተጠንቀቅ እንደቆሙ እናውቃለን። እነዚህ ዜጎች ከሁሉም የእምነት የቋንቋ  የጾታ የእድሜ  የኑሮና  የማህበረሰብ ስብጥር የሚያካተቱ  እንደሆኑ እናውቃለን። በሃገሪቱ ታሪክ ተሰምቶና  ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ  የወታደር ልብሱን  እየጣፈ እንዲለብስ፣  የወታደር ጫማውን መቀየሪያ አጥቶ  ሸበጥ እንዲያደርግ የተገደደውን፣  የወያኔ ጀነራሎች በስልጣንና  በዘረፋ ሲያብጡ በድህነት እንዲሟሽሽ የተፈረደበት የሃገሪቱ ሰራዊት በዘር በእምነት ሳይለያይ ከህዝባዊ ሃይሉ ጎን ለመቆም አሰፍስፎ  የቆመ  እንደሆነ  እናውቃለን። ይህ ሃገራዊ እውነታ ለህዝብ የገባነውን ቃልኪዳን የለምንም ጥርጣሬ  ማስከበር እንደምንችል በሙሉ ድፍረት እንድናውጅ የሚያስችለን ሃቅ ነው።

የወያኔ ጀንበር እየጠለቀች የኢትዮጵያ  ህዝብ ጀንበር እየፈካች የመሄዱ ጉዳይ እንደማይታጠፈው  የመንጋትና  የመምሸት የተፈጥሮ ህግ ነቅነቅ የማይል እንደሆነ ግንቦት7 ጠንቅቆ ያውቃል።  እውቀታችን ልዩ ጥበብ የሚጠይቅ ኣይደለም። ግፍ ፍትህን አሸንፎ፣ እውነት በሃሰት ተደፍቃ፣ ጥላቻ ፍቅርን፣ አድሎ እኩልነትን፣ ሃገራዊ ክህደት ሃገር መውደድን፣ ባንዳነት አርበኛናትን ለዘላላሙ ቀብረው የሄዱበት የሃገራችንና  የሰው ልጆች ታሪክ የለምና የወያኔን አይቀሬ ሞት ለመተንበይ  ልዩ ጥበብ አያሻንም። ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን በዘረፋና በጥላቻ  የደነዘዘ ህሊና ያዳበሩት የወያኔ  ባለስልጣናትም ያውቁታል። ያለእኔ  ጀግና የለም፣ ያለእኔ  አልሞ  ተኳሽ የለም በሚል እብሪት በመጻደቅ የሚታወቁት ወያኔዎች በመቶ ሽዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ተከበው፣  በታንክ በአይሮፕላን በሚሳይል ታጅበው ከሚኖሩበት ቤተመንግስትና ቪላዎች ውስጥ ብርክ እንዲይዛቸው ያደረገው ለመሆኑ፣  ሳር ቅጠሉ ግንቦት ሰባት እየመሰላቸው ሲበረግጉ እንደሚያመሹ፣  የግንቦት ሰባት አባላት እያሉ ከድርጅታችን ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች እያሰሩ ሲያሰቃዩ ፣  ከምላሳቸው ላይ ግንቦት 7  የሚል ስም ተፈናጦባቸው  እንደሚውሉ በራሳቸው ሚድያ  ወያኔዎች ራሳቸው እያሳዩን እያስደመጡን ነው። ከዚህም አልፎ በዚህ አንድ አመት ውስጥ  የህዝባዊ ሃይሉን መሪዎች በመግደል ድርጅቱን ለማኮላሸት ይቻላል በሚል ወያኔ የላካቸው ነፍሰ ገዳዮችና ድርጅቱን ከውስጥ ለመቦርቦር ያሰማራቸው ሰርጎገቦች ተራ በተራ ተልእኳቸው እየከሸፈ በህዝባዊ ሃይሉ እጅ እየወደቁ ወይም ተልእኳቸው እንደማይሳካ ሲረዱ እየፈረጠጡ ወደ ወያኔ ሲመለሱ አይተናል።

ያለፈው አንድ አመት ተመክሯችን ስለወያኔ  ብቻ ሳይሆን ስለራሳችንም ጥንካሬና  ድክመት ብዙ ነገሮች ያስተማረን ኣመት ነው። የቀደምቶቻችን የጀግንነት የአርበኛነት ቅርስ በመላ ህዋሳቸው የተሸከሙ  ለኢትዮጵያ እና  ለህዝቧ ሲሉ ደማቸው ለማፍሰስ ውድ ህይወታቸውን ለመሰዋት ወደኋላ የማይሉ ቆራጥ ብቻ ሳይሆኑ አርቀው የሚያዩ  በርካታ ልጆች  ሃጋሪቷ ያሏት መሆኑን ያረጋገጥንበት አመት  ነው።  በሌላ በኩል ደግሞ  ድርጅታችን የኢትዮጵያን ህዝብ ብቸኛው የመንግስት ስልጣን ባላቤት የማድረጉን ታሪካዊ ራእዩን ለመሳካት የሚያደረገው ትግል ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ጋር የሚደረግ እንደሆነ  በሚገባ  የተረዳነው  በዚሁ የአንድ አመት የድርጅታችን እድሜ  ነው። ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል ወያኔ በማህበረሰባችን ውስጥ ከዘራቸውና የሃገሪቱን ዜጎች እንዲበክሉ ካደረጋቸው የዘረኛነት የአድሎ  ከህዝብና  ከሃገር ጥቅም በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም፣ የሱሰኛነትና የሙስናና ሌሎችም አደገኛ ባህሎች ጋር ነው።

ህዝባዊ ሃይሉ ደግሞ  ደጋግሞ  እንደገለጸው ትግላችን አንድ መንግስታዊ ስርአት ወድቆ ሌላው የመንግስት ስርአት በመጣ ቁጥር የህዝብ ተስፋ እየጨለመ  “አዲስ ከመጣው ስርአት ያላፈው ያረጀ ስርአት በግፈኛነቱ በዘራፊነቱ ያነሰ ነበር” የሚል የግፈኛና የዘራፊ ስርአቶች ንጽጽር ላይ የቆመ አሳዛኝ የህዝብ ህይወት እንዲያበቃ ነው። ደርግን ያየ የአጼውን ስርአት እንከኖች ረስቶ ንጉሱ ይሻሉን ነበር ያለበት፣ ወያኔን ያየ የደርግን አስከፊ ዘመን ረስቶ መንጌ በስንት ጣሙ ያለበት አሳዛኝ ሁኔታ ከወያኔ መውደቅ በኋላ በሃገራችን እንዳይደገም ነው ትግላችን። የኢትዮጵያ ህዝብ የውድ ልጆቹን ህይወት ገብሮ ወያኔን በማስወገድ የሚያመጣው ስርአት ከወያኔ ብሶ ህዝብ ወያኔ ማረኝ የሚልበትን ቅስም ሰባሪና አዋራጅ የታሪክ ቅጥልጥሎሽ  እንዳይቀጥል ማድረግ ህዝባዊ ሃይሉ የተመሰረተበት፣ አባላቱ መከራ ለመቀበልና መስዋእትነት ለመክፈል በረሃ የገቡበት ዋናውና ብቸናው ምክንያት ነው። ትግላችንን መራራ የሚያደርገው ከበሰበሰውና የአንድ ጀምበር የህዝብ ቁጣ ከታሪክ ቆሻሻ የመጠያ ስፍራ ከሚከምረው  የወያኔ ስርአት ጋር ብቻ ሳይሆን በወያኔ ቦታ የሚተካውን ስርአት ከአድሎና ከዘረኛነት ከዘረፋና ሃገራዊ ክህደት የጸዳ፣ ዳግም ለኢትዮጵያውያን ውርደትና እንግልት ምክንያት እንዳይሆን ለማድረግ ከራሳችን ጋር ሳይቀር የማያቋርጥ ትግልን ማድረግ የግድ ስለሚል ነው። ህዝባዊ ሃይሉ የአመጽ ትግል የሚያደርግ፣ የመሳሪያው ብዛትና  የሰራዊቱ ቁጥር እያደገ  የሚሄድ ሃይል መሆኑን ስለምንረዳ  ይህን ሃይል ገና ከጅምሩ ከብዙ እንከኖች እያጸዱ ማደራጀት ካልተቻለ  በሃገርና በህዝብ ላይ የሚመጣውን አደጋ  የህዝባዊ ሃይሉ አባላት ጠንቅቀው የተረዱት ሃቅ ነው። ይህ ግንዛቤ የሰራዊቱን አባላት በጥንቃቄ መመልመልን፣ ማሰልጠንንና መገንባትን የግድ የሚል ነው።

ይህ ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል እጅግ መራራ ነው። ታሪካዊ ስህተቶችን ላለመድገም የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ትግል የአካልና የመንፈስ ጽናትን፣ ሃቀኛነትን፣ ታማኝነትን፣ ጀግንነትን የሚጠይቅ ትግል ነው። የወያኔ ስርአት ከሃገር ግድያው በተጨማሪ ትውልድን ለመግደል ሆን ብሎ ያስፋፋቸው እኩይና ጎጂ ባህሎችና ልምዶች ምን ያህል ማህበረሰባችንን እንደጎዱት ህዝባዊ ሃይሉ ባላፈው አንድ አመት እድሜው በሚገባ የተረዳው ጉዳይ ሆኗል። ህዝባዊ ሃይሉ የሚመኘውን የኢትዮጵያ ትንሳኤና ተሃድሶ እውን ለማድረግ እነኝህ  ወያኔ ሆን ብሎ  ያስፋፋቸውን የባህልና የሞራል ብክለት ማጽዳት የግድ እንደሆነ የተረዳ አካል ሆኗል።

ትግላችን መደፍረስን መጥራትን፣ መንተክተክን መስከንን የትግሉ ሂደት አካል አድርጎ  የሚጓዝ ነው።   ትግሉ የሚልመጠመጠውን እንደቀስት ቀጥ ብሎ ከሚራመደው፣ በካፊያው የሚንቀጠ ቀጠውን ለዶፉ ደንታ ከሌለው፣ ዝናር በቅፌን ከምሩ ተኳሽ  የሚለይ መራራ ትግል ነው። ያለፈው አንድ አመት ይህን አስተምሮናል። ህዝባዊ ሃይሉ ትግሉ ቀላል ነው የሚል ከእውነታ ጋር ያልተያያዘ ቃል ለህዝብም ሆነ ህዝባዊ ሃይሉን ሊቀላቀሉት ለተዘጋጁት ወገኖቹ አይናገርም። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል ለተሰለፉ በሽዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ትግሉ የሚጠየቅውን የሞራል የስብእና ጥብቅነት፣ከፍተኛ  የሃገርና የወገን ፍቅር፣ ጥልቅ የሆነ የመስዋእትነት ፈቃደኛነት የሚጠይቅ መሆኑን ከማስረዳት አንቦዝንም። ህዝባዊ ሃይሉ ለህዝብ ቃል እንደገባው ከወያኔ  ጋር የምናደርገው ትግል በጥበብ በእውቀት በጥናት በጥንቃቄ የምናደርገደው ነው። ነጻነት ያለመስዋእትነት እንደማይሳካ ብናውቅም ለተራ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስንል በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የሃገሪቱን ውድ ልጆች በከንቱ የሚማግድ ጀብደኛ እንቅስቃሴ  አናደርግም። የውሸት ተስፋ  ህዝብን አንመግብም።  አይናችንን ከዋናው የኢትዮጵያና  የህዝቧ  ጠላት ከሆነው ከወያኔ ላይ አንስተን በሌሎች  ወያኔን እቃወማለሁ በሚሉ ሃይሎች ላይ አንተክልም። ከወያኔ ሌላ ወደ ጎን የምንዋጋው፣ የምንጨቃጨው አታካራ የምንገጥመው ምንም ሃይል አይኖርም። ወያኔን ለመምታት ህዝባዊ ሃይሉ የጨበጠው  ቡጢ ወገኖቻችን በፍቅር ለመጨበጥ የሚዘረጉ ጣቶች  እንዳሉት በጸረ ወያኔ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ  ከልባቸው ለመተባበር ለሚፈልጉ ሃይሎች ሁሉ ግልጽ እናደርጋለን።

ያለፈው አንድ አመት የመሰባሰብ የድርጅት ምስረታ  መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካና የወታደራዊ  ስልጠና የተሰጠበት፣ የድርጅት ማጠናከሪያና የማጥራት ሂደት የተካሄደበት ነው። በዚህ ረገድ የተሰራው ስራ አጥጋቢ ውጤት አስገኝቷል። ስልጠናው፣ ድርጅት ማጠናከሩና  ማጥራቱ ወደፊትም የሚቀጥል ነው። መጪውን አመት የተለየ የሚያደርገው ህዝባዊ ሃይሉ በህዝብ ላይ በሚደርሰው ግፍና ውርደት ከሚሰማው ከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት አልፎ ባላፈው አመት ሊደርስላቸው ያልቻለውን የሃገራችንን ግፉአን ህዝቦች መታደግ የሚችልበትን እርምጃዎች መውሰድ የሚችልበት አመት መሆኑ ነው። በዚህ የህዝባዊ ሃይላችን የአንደኛ አመት ምስረታ  ክብረ በአል ወቅት ወገንም ጠላትም በግልጽ እንዲያውቀው የምንፈልገው ይህን ሃቅ ብቻ ነው።

ውድመት ለዋናውና  ለብቸኛው የኢትዮጵያ ህዝብና  የኢትዮጵያችን ጠላት ለሆነው የወያኔ ገዥ ጉጅሌ!

ድል በወያኔ ግፈኛ ስርአት አበሳውን ለሚያየው የመላው የኢትዮጵያ  ህዝብ!

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል
Ginbot 7 Popular Force
www.ginbot7pf.org
Tel: +44 208 123 0056
email: [email protected]