0
Posted April 13, 2013 in News
 
 

በህዝብና በሀገር ላይ ቀልድ የለም (በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ስብስብ)


በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ስብስብ የተሰጠ የተቃዉሞ መግለጫ

ህዝባችን መስዋእትነት ከፍሎና ተንከባክቦ ባቆያትና እትብቱ በተቀበረባት ምድር የመኖር ነፃነቱን ከተነፈገ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን በዘርና በቋንቋ እየተመነዘረ በገዛ ሀገሩ እንደ ባይታዋር ተቆጥሮ ከተባረረና ሜዳ ላይ ከተጣለ፡- ሀገር አለኝ ማለቱ ትርጉሙ ምንድን ነው?። የውጭ ባለሃብቶች ለም መሬታችንን ይዘው ኰርተውና ተንደላቅቀው ሲያርሱና ሲያለሙ በአንፃሩ የሀገሩን ባለቤት የሆነውን ህዝብ የበይ ተመልካችና ተመፅዋች ሆኖ እየተንከራተተ የሚኖረው እስከ መቼ ይሆን?። ይህ ዓይነቱ አሳፋሪ እርምጃ እየተደጋገመ ከሄደስ የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል? ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ስርዓተ አልበኝነት ነግሶ ህዝቡ አቤት የሚልበት የፍትሕ ቦታ አጥቶ ሲተራመስ ስናይ ለመሆኑ በሀሪቱ ላይ መንግስት አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል።

ሰሞኑን በቤንሻንጉል አካባቢ በሽዎች በሚቆጠሩት የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰው ከቤት ንብረታቸው የማፈናቀል ድርጊት በተለያዩ ሚዲያችና እንዲሁም ሜዳ ላይ ከወደቁት ተፈናቃዮች ከራሳቸው አንደበት ስንሰማ እጅጉን አሳዝኖናል። ይህ አረሜናዊ ድርጊት ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል መንግስት ቀርቶ በባዕዳን ወረራ ጊዜም ቢሆን ያልተፈፀመና በኢትዮጵያ የመንግስታት ታሪክም ታይቶ የማይታወቅ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን አሳይቶናል። ከዚህም አልፎ የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ደግሞ ድርጊቱን መፈፀሙ ብቻ ሳይሆን የህወሓት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት እንደ ለመዱት ሁሉ ወንጀሉን ለመሸፋፈን ሲሉ የሰጡትን መግለጫ በህዝቡ ህይወት ላይ መቀለድና ማፌዝ መሆኑን በይፋ አሳይቶናል። ሰለሆነም ፡-

1. የህወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት በወገኖቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው አረሜናዊ ድርጊት ኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር ያልተከተለ፣ የህዝባችን ሕገ መንግስታዊና ዜግነታዊ መብት የሚጥስ፣ ዓለም አቀፋዊ የሰብኣዊ ፍጡር አያያዝ የሚፃረር የወንጀል ድርጊት በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን። በዚሁ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሳተፉ ሰዎችም በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን።

2. “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” ነውና የዜጎች ህይወት የዶሮን ያህል ክብር ሳትሰጡ ሀገርንና ህዝብን በፍርፋሪ፣ በስልጣንና በጊዚያዊ ጥቅም በመለወጥና እንዲሁም የህዝቡን ትዕግስት፣ ጨዋነትና ዝምታ እንደ ሞኝነት በመቁጠር በየዋሁ ህዝባችን ላይ ወንጀል እየፈፀማችሁ የምትገኙ የስርዓቱን ካድሬዎችና ደጋፊዎች ሁሉ ትዕግስት ገደብ አለውና የዛሬ ዝምታ የነገ እሳተ ጎሞራ እንደሚሆን ተገንዝባችሁ ከእኩይ ድርጊት እጃችሁን እንድታነሱ እንጠይቃለን።

3. በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለው የወንጀል ድርጊት እንደ ተለመደው “የባሰ አታምጣ” ተብሎ በማድበስበስ፣ በዝምታና በማዳፈን የሚታለፍ ሳይሆን ጉዳዩን ገለልተኛ አካል እቦታው ድረስ ሂዶ እንዲያጠራ ዓለም አቀፍ ሰብኣዊ መብት ተሟጓች ድርጅቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

4. በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስፓራ የምትኖሩ ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ በመካከላችን ሊኖር የሚችለው የአመለካከት ልዩነት እንደ ባላንጣነት ሳይሆን እንደ ውበት ተቀብለን ለጋራ ችግር በጋራ መቆም ጊዜው የግድ ይለናል። ካልሆነ ግን በተናጠል ተበታትነን በየተራ እየተደቆስን መኖር የማይቀር ነው። ስለዚህ “ጎርፍ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ የህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች ቀለማቸውን እየቀያየሩ በልማት ስም የህልም እንጀራ ለማብላትና መርዝ በማር ጠቅልለው ለማጉረስ ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው ሲንቀሳቀሱ እኛ ደግሞ የህልውናችን ሞሶሶና ዋስትና በፍቅር፣ በመከባበር፣ በመደማመጥና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነት በተግባር ማሳየት ለነገ የማይባል የያንዳንዳችን አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን በፅኑ እናምናለን።

5. ኢሕአዴግ በተለይም ዕድሜ ልኩን ያንተ ነፃ አውጪ ነኝ እያለ በትግራይ ህዝብ ስምና ደም ሲነግድ የኖረው ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) በተለመደው ባህሪው በወንድሞቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው ጭካኔ የተሞላበት አረሜናዊ ድርጊት ሆን ተብሎ ወገን ከወገኑ ጋር ለማጋጨትና ጥርጣሬ ለመፍጠር የተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ከተገነዘበው ውሎ አድረዋል። ስለዚህ ህወሓት በኢትዮጵያውያን መካከል እየተከለ ያለው ልማት ሳይሆን ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የጥፋት ፈንጅ መሆኑን በመገንዘብ የአንድነትና የሰላም ባላንጣ የሆነውን ድርጅት የሚፈፀመው ግፍ ከካድሬዎቹ በስተቀር ብዙሃኑን የማይወክል መሆኑን እየገለፅን ቡድናዊ አምባ ገነኖችን ከህዝብ ነጥሎ መታገል የፓለቲካ ብልህነት ብቻ ሳይሆን አማራጭ የሌለው የለውጥ መንገድም እሱ ብቻ መሆኑን እናምናለን።

6. እኛም ከማንም ከምንም በላይ ዘር፣ ቦታ፣ ሀይማኖት፣ ቋንቋ፣ የፓለቲካ እምነትና ስደት ሳይገድበን ከ80 ሚሊዮን በላይ የሆነውን ህዝብ እንደ ዓይን ብሌናችን በማየት ችግሩ ችግራችን፣ ደስታው ደስታችን፣ ሀዘኑም ሀዘናችን መሆኑን በማመን የጋራ ችግራችንን በጋራ ለመፍታት በሚደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ ከጎኑ የምንቆም መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ እናረጋግጣለን።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ለዘላለም ትኑር