0
Posted January 16, 2013 in News
 
 

አንድ ለአምስት የልማት ወይስ የፖለቲካ ሠራዊት?


አለቃ ገብረ ዮሐንስ አባዲ ይባላሉ፡፡ ዕድሜያቸው 39 ሲሆን፣ የስድስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በትግራይ ክልል ደጉዓ ተምቤን ወረዳ አረጌ በሚባል ቀበሌ አካባቢ ይኖራሉ፡፡

የሚተዳደሩት በግብርና በመሆኑ ሞዴል ገበሬ (ሞዴል ሐረ ስታይ) ናቸው፡፡ ገበሬ ብቻም አይደሉም፡፡ ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት የቀበሌው የወጣቶች ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው ሲሠሩ ነበር፡፡ ‹‹ዓዲ ሐርሐር›› በመባል በሚታወቀው 25 አባላት ባሉት ‹‹የልማት ቡድን›› ታቅፈውም ሠርተዋል፡፡ አምስት አምስት በመሆን በአምስት አነስተኛ ቡድኖችም የተከፋፈለ ነው፡፡ እያንዳንዱን ቡድን አንድ የሕወሓት አባል (ካድሬ) ይመራዋል፡፡

የልማት ወይስ የፖለቲካ ቡድኖች? 
አለቃ ገብረ ዮሐንስ ያሉበት ቡድንን ጨምሮ ‹‹የልማት ቡድኑ›› ዓላማ ገበሬዎች ማዳበርያ እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል፣ አዳዲስ ምርጥ ዘሮችንና አዳዲስ የእርሻ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ፣ በመስኖና በሌሎች የእርሻ ሥራዎች ገበሬዎች እርስ በርሳቸው ተሞክሮአቸውን እንደለዋወጡ ማገዝ ነው፡፡

የአካባቢው አስተዳደርና የሕወሓት የወረዳው ጽሕፈት ቤቶች እነዚህን ቡድኖች ሲያቋቁሙ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ዓላማዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ገበሬዎችን አሳምነዋል፡፡ አቶ ገብረ ዮሐንስም በእዚህ ቡድን ውስጥ በመሳተፍ አላቅማሙም፡፡ ቀስ በቀስ ግን የተባለው ሌላ የሚሠራው ሌላ እየሆነባቸው መምጣቱን ደግሞ ይናገራሉ፡፡

‹‹ገቢያችንን ከፍ ለማድረግ ስለሚጠቅም እንዲህ መሰባሰቡን መጀመርያ አልጠላነውም፡፡ ኑሮአችንን ለማሻሻል አንዳችን ከሌላችን እየተመካከርን መሥራት ጀምረን ነበር፡፡ ወደኋላ ግን ዓብይ ችግር እየሆነ መጣ፡፡ ከምንሠራበት የምንሰበስብበት ይበልጣል፡፡ ሁሌም መገማገም ነው፡፡ አንድ ሰው የሚገመገመው ደግሞ በሥራው ብቻ አይደለም፡፡ አስተሳሰቡ ምን ይመስላል? ዓረና ከሚባሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት አለው ወይ? በአብዛኛው ከእነማን ጋር ይገናኛል? ምን ያወራል?›› በማለት ይዘረዝሩ ጀመር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በአብዛኛው ጊዜ የሚወራው ስለተደራጁበት ዓላማ ሳይሆን ፖለቲካ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዓላማውም ተለውጦ የእያንዳንዱን የቡድኑን አባል የፖለቲካ አቋም ማጥራት ነው፡፡ ሌሎችንም ማሳመን፡፡

አቶ ገብረ ዮሐንስና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ስለ ሥራ መነጋገር እየቀረ መሰባሰቡ ቋሚ እየሆነ መምጣቱ አላስደሰታቸውምና በግምገማ ተቃውሞአቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም የዓረና አባላት ተብለው ሲነቀፉ በየትኛውም ቡድን አባል ላለመሆን ወስነው ጥለውት መውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚያ በፊት ዓረና የሚባል ነገር እንደማያውቁ፣ አሁን ግን እነርሱን የሚቃወም አካል መሆኑን አውቀዋል፡፡ የወጣቶች ማኅበር ሊቀመንበርነትም በራሳቸው ፈቃድ ትተውታል፡፡ ሕዝቡን ፖለቲካ ሲያስተምሩ የሚውሉና ማን ምን እንዳለ መረጃ ሲያቀብሉ የሚውሉ የቡድኖች ኃላፊዎች እንደሚደረጉም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ከዚህ ውጪ ችግር አለ፣ አካሄዱ ትክክል አይደለም ብሎ የሚከራከር ሰው አይፈለግም፡፡ እንደጠላት ይታያል፡፡ ሁሌም በጥርጣሬ ዓይን ይታያል፤›› ይላሉ፡፡

በአካባቢው የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያ የሆነ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ግለሰብ ጉዳዩን አስመልክተን አነጋግረነው ነበር፡፡ አደረጃጀቱ ‹‹ኔትወርኪንግ›› እየተባለ ነው የሚጠራ ብሎናል፡፡ በአካባቢው ኔትወርኪንግ የተጀመረው በምርጫ 2002 መሆኑን፣ ሙሉ ለሙሉ ለምርጫ ቅስቀሳና ማስተማር ጥቅም ላይ መዋሉን ይናገራል፡፡ በአካባቢው ቋንቋ (ትግርኛ) አጠራር ‹‹ልምዓት ጉጃለ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ የልማት ቡድን እንደ ማለት ነው፡፡ የእርሻ ባለሙያውም እንደሚሉት፣ እነዚህ ቡድኖች የተቋቋሙበት ዓላማ የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ታስቦ ነው፡፡ ‹‹መሬት ላይ በተግባር የሚሠራው ግን ሌላ ነው፡፡ ከእርሻ ሥራዎች የድርጅቱ የፖለቲካ ሥራዎች ይበዛሉ፡፡ ከሚሠሩ ሥራዎች የአባልነት መዋጮ መሰብሰብ፣ ስለ ድርጅቱ (ሕወሓት) ማስተማር፣ የድርጅቱ ልሳኖችን መበተንና ክፍያ ማስፈጸም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ ዓዲጉደም (ደቡብ ምሥራቅ ዞን) የግብርናን ኤክስቴንሽን ልማትን አስመልክቶ በተካሄደ ስብሰባ ጉዳዩ ተነስቶ እንዳነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹የተሰጠው ምላሽ ደስይልም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹አንድ አስተሳሰብ ካልፈጠርን ልማት ብሎ ነገር የለም፤›› የሚል ምላሽ ከክልሉ ባለሥልጣናት እንደተሰጣቸው በመግለጽ፡፡

አንድ የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ በቅርቡ በክልሉ የሴቶችን ማበረታቻ (Women Empowerment Project) በተመለከተ ለማየት ወደ ክልሉ ናዳር ዓዴታ ወረዳ ጣቢያ (ቀበሌ) ደብረ ገነት ተጉዛ ነበር፡፡ የሴቶች የልማት ፕሮጀክት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ ጤና፣ መሠረተ ትምህርትና ኮሚኒቲ ኮንቨርሴሽን በተመለከተ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች የሚታገዙ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ የሚሆኑት በዚሁ አንድ ለአምስት አደረጃጀት ነው፡፡ ሥራው እንዲቀላጠፍ መልካም መሆኑን ባልደረባችን ተገንዝባለች፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ግን አንድ ዓይነት እንዲሆኑ መደረጉንም እንዲሁ፡፡ ‹‹በዚሁ አንድ ለአምስት ያልተደራጀ መኖር እንዳቆመ ነው የሚቆጠረው፤›› ብላለች ምልከታዋን ስትገልጽ፡፡ ከምንም ዓይነት አገልግሎት የሚገለል ይሆናል፤ የተለየ እንግዳ አስተሳሰብ ያለው ሰው ተደርጎም ይታያል በማለት፡፡

በአማራ ክልል አንዳንድ ወረዳዎችም አደረጃጀቱ ትግራይ ውስጥ እንደተመለከተችው ጠንካራ ባይሆንም ተመሳሳይ ነገር አስተውላለች፡፡

አንድ ለአምስት እንደ ኪራይ ሰብሳቢነት 
ኢሕአዴግ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ደረጃ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ብዙ ብሏል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሰዎች በትክክል ምን ማለት እንደሆነ በውል አይገነዘቡትም፡፡ በቴሌቪዥን ወይም ደግሞ በሬዲዮ በሚተላለፉ የመንግሥት ዘገባዎች ይህ ጽንሰ ሐሳብ ሳይጠቅስ አይቀርም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ፣ ወዘተ በልማታዊ አስተሳብ መቀየር እንዳለባቸው በስፋት ይነገራል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ሥልጣንን ተገን አድርጎ የተለያዩ ሰዎችን ያልተገባ ጥቅም የሚያገኙበት አካሄድ ከሆነ ከሙስና የሚለይበት መስመር አይታይም፡፡ ያም ሆነ ይህ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዶክትሬት ዲግሪያቸው መመረቂያ ጽሑፋቸው የተከራከሩበት ልማታዊ መንግሥት ስለመፍጠር ነበር፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ እንዲነግሥ የተፈለገው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ራሱ ግን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች ይስተዋሉበታል ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ የሚሰባሰቡ አባላት፣ ባለሀብቶች፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በብዙዎች የኢሕአዴግ አጀንዳ አራማጆች ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህም መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከኅብረተሰቡ ውስጥ በማጥፋት ስም እየዘረጋው ያለው አስተሳሰብ ራሱ የመንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› እየፈጠረ እንደሆነ የሚያምኑ ይበዛሉ፡፡ የመንግሥትን ሀብት ለጥቅም በማቅረብ አባላትንና ደጋፊዎችን እያፈራ መሆኑን በመጠቆም፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲጠፋና ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲያነግሥ በስፋት እየተሠራ ያለው በአንድ ለአምስት አደረጃጀት መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ በገጠርም በከተማም በተለያዩ ዘርፎች እየተደራጁ ያሉት የልማት ቡድኖች ‹‹ልማታዊ ሠራዊት›› ለመፍጠር መሆኑ ከባለሥልጣናት አንደበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ አወቃቀሩም ከጦር ኃይል አደረጃጀት የተወሰደ ሲሆን፣ የሚፈለገውን ልማት ለማሳካት አንድ ዓይነት የጠራ አመለካከትን መፍጠርን ያለመ ነው፡፡ አጀንዳውም እሱ ነው፡፡ ፅንሰ ሐሳቡ በሌላ አገር ይሠራበት አይሠራበት ግን ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡

ጥያቄው መንግሥት የልማት ጠንቅ አድርጎ የሚመለከተውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ለመተካት እየፈጠረው ያለው ይኼው አደረጃጀት፣ እውነት የልማት አስተሳሰብ ነው ወይስ ሥልጣን ላይ ያለው አካል የፖለቲካ አጀንዳውን በኅብረተሰቡ ለማስረፅ እየተጠቀመበት ነው የሚል ነው፡፡

በቅርቡ ቀጣዩ የአካባቢና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሜዳውን ለማስተካከል በአንዳንድ አገራዊ ጉዳዮች እንነጋገር በሚል 18 ጥያቄዎች ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱና ዋነኛ ጥያቄያቸው ይኼው አደረጃጀት ነው፡፡ የፒቲሽኑ ፈራሚ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ፣ አንድ ለአምስት በሚባለው አደረጃጀት መላውን ሕዝብ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት እንዲኖረው እየተሞከረ ያለው አካሄድ ነው ብለዋል ለሪፖርተር፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች መካከል መድረክና መኢአድ ምርጫ 2002 እንዲደገም ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ ያቀረቡዋቸው ማስረጃዎች መራጮች በዚሁ በአንድ ለአምስት ተደራጅተው መምረጣቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡

ይኼው ተቀባይነት ያላገኘው ቅሬታ ግን በአንዳንድ ጋዜጦች በወቅቱ የተዘገበ ሲሆን፣ ገለልተኝነታቸውን ሁሌም አወዛጋቢ የሆነው ፍርድ ቤትና ምርጫ ቦርድ ቅሬታዎቹን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡ አሁንም ምርጫ ከመድረሱ በፊት ለመነጋገር ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ የሆነባቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች ይኼው ‹‹የልማታዊ ሠራዊት›› ግንባታ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እየዋለ መሆኑን ማስረጃ አለን በማለት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

ጊዜያዊ ኮሚቴው ካቀረበው አንድ ማስረጃ ‹‹በደቡብ ክልል አርቤጎና ወረዳ የምርጫ ሥራ ለማሳካት የወጣ አጭር ማስፈጸሚያ ቼክ ሊስት›› በሚል በአርቤጎና ወረዳ የደኢሕዴን ን/ቅ/ጽ/ቤት የተዘጋጀና ሾልኮ የወጣ የተባለ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ የሕዋስ ዕቅድ አደረጃጀትን አስመልክቶ፣ ‹‹አንድ አባል 4-5 ደጋፊዎቹን በማስተካከል መልኩ እንዲዘጋጅ ማድረግ›› ይልና፣ ‹‹ለልማት የፈጠርነውን የልማት ሠራዊት ወደ ምርጫ ተግባር በማዟዟር ምርጫውን በድል የምንወጣበት አግባብ መፍጠር›› ማስፈለጉን ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በመምህራንና ለመራጭነት በደረሱ ልጆች፣ በልማት ሠራተኛና በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በመታገዝ በእነርሱ አማካይነት የቤት ለቤት ሥራ መሥራት ማስፈለጉንም ኮሚቴው አገኘሁት ያለው ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በኮሚቴው ገለጻ መሠረት ይህ አደረጃጀቱ እንዴት ለምርጫ ጥቅም እንደሚውል የሚያሳይ ነው፡፡

የጊዜያዊ ኮሚቴው አባል ያልሆነው ኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ እንደሚሉት፣ መንግሥት ለልማት ሥራ ምንም ዓይነት አደረጃጀት መጠቀሙ አይጠላም፡፡ ‹‹ችግሩ መደበላለቁ ነው›› በማለት በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ምንም ልዩነት በሌለበት አገር ገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥራዎቹን በሙሉ እያከናወነ ያለው በመንግሥት ሀብትና በመንግሥት መዋቅር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይኼንን አንድ አምስት የሚል አደረጃጀት ኢሕአዴግ የራሱን ፖለቲካ ለማራመድ እየተጠቀመበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሥራ አጥነት ትልቅ ችግር በሆነበትና ትልቁ ቀጣሪ መንግሥት በሆነበት አገር፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች በዚሁ ዓይነት መንገድ እንዲደራጁ ማስገደድ ቀጥተኛ ይልሆነ የነፃነት ገፈፋ ነው ይሉታል፡፡ ‹‹መከላከያው፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቱና ምርጫ ቦርዱ ገለልተኛ ባልሆነበት አገር ደግሞ ችግሩ የጎላ ይሆናል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የተቃዋሚዎች ደጋፊ ወይም አባላት በሆኑት ይቅርና ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ የማይፈልጉ ዜጎች በግዴታ አማራጭ ሐሳብ ሳይቀርብላቸው አንድ አመለካከት እንዲጫናቸው እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡ ኢሕአዴግ ከእንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲታቀብ በማሳሰብ፣ አንድ ቀን ያልተፈለገ ተቃውሞና አመፅ ሊያስከትል ይችላል ይላሉ፡፡ ይህንን ሥጋታቸውን የሚገልጹት አቶ ሙሼ፣ ሥራው በሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ማኅበራት ሊሠራ ይችላል የሚል አማራጭ መፍትሔ ሐሳብም ያቀርባሉ፡፡

አንድ ለአምስት ያሸልማል
በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል የተለያየ ትርጓሜ እየተሰጠው ያለው ይኼው አደረጃጀት በድብቅ የሚሠራ አይደለም፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ልማታዊ ሠራዊት ተፈጻሚ የሚሆንበት ማንዋል ተዘጋጅቶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በገጠር አካባቢ የተለያዩ የመስኖና የጤና ኤክስቴንሽን ሥራዎችን ለማስፈጸም እየዋለ ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን ለፖለቲካ አጀንዳ መዋሉ ይነገራል፡፡ አቶ ሬድዋን ሁሴን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ የአማካሪ ሚኒስትር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት የተመቸውን አደረጃጀት መጠቀም ይችላል፡፡ መብቱም ነው፡፡ ኢሕአዴግ የተደራጀ ሕዝብ ጉልበት አለው ብለው ያምናል፡፡ ‹‹ገጠር ውስጥ ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ አሁንም ከተማ ውስጥ እንገባለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት ለምርጫ ትጠቀማላችሁ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በአጋጣሚ ሆኖ ሥልጣን ላይ ያለ አካል የመንግሥት አደረጃጀትና ሀብት መጠቀሙ አዲስ ነገር አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሰኔ 2004 ዓ.ም. በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የተዘጋጀው ‹‹በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ የሠራዊት ግንባታ›› በሚል የተዘጋጀው ማንዋል፣ በየደረጃው የልማት ሠራዊት ለመገንባት የሚያስፈልግ አካሄድ የሚጠቁም ሲሆን፣ ዓላማውም የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ ለማጥፋት ነው ይላል፡፡ በአብዛኛው በማንዋሉ የቀረበው ጽሑፍ ይዘት ምንም ክፋት የሌለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን በአጀንዳው ‹‹መካከለኛ ባለሀብቶች በስፋት የሚፈጠሩባቸው አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በመሆናቸው፣ በልማታዊ አስተሳሰብ የተቃኙ ተቋማትን ከወዲሁ መገንባት በቀጣይ ልማታዊ ባለሀብቶች መበራከት ብሎም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው፤›› ነው ይላል፡፡ የዛሬ 20 እና 30 ዓመት ጭምር ‹‹ልማታዊ›› አስተሳሰብ ያላቸውና የኢሕአዴግ ደጋፊ አካላትን ከወዲሁ ለማፍራት ያተኮረ ይመስላል፡፡ በዚሁ አደረጃጀት የታቀፉ ሠራተኞች ከ70 እስከ 80 በመቶ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሥራ እንዲያውሉ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ለማስረፅ በሚል የተሰጠው ጊዜ ይህንን አስተሳሰብ ከኢሕአዴግ የፖለቲካ አጀንዳ ጋር እየተጣመረ በመሆኑ ጥያቄውን የበለጠ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ተቃዋሚዎች ይከራከራሉ፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በቅርቡ በ22 ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ባካሄደው የሪፎርም ግምገማ የመልካም አስተዳደር ለውጥ አለመምጣቱን ገልጿል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ሙክታር ከድር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ ለውጥ ላለመምጣቱ በምክንያትነት ያስቀመጡት የአንድ ለአምስት አደረጃጀት አለመሳካትን ነው፡፡ አደረጃጀቱ ሦስቱ ክንፎች የያዘ ሲሆን የኢሕአዴግ ክንፍ፣ የመንግሥትና የኅብረተሰብ ክንፍ በሚል የተቀመጠ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡