0
Posted January 13, 2013 in News
 
 

“የኑ እና እዩኝ” ኑዛዚያዊ የወያኔ ጥሪ


የህዝብ ድጋፍ የሌለው  የመከላከያ ሠራዊት በየትኛውም አለም ቢሆን ለድል የበቃበት ጊዜ አናሳ ነው። ወያኔዎች ሰሞኑን ከእየአቅጣጫው የተፈጠረባቸውን ውጥረት ለማላላትና ለማስተንፈስ ይረዱኛል ያሏቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች “የኑ እና እዩኝ ኑዛዚያዊ ጥሪ” እያቀረቡ ነው።

እርግጥ ነው ሰራዊቱ በቡሬ ግንባር በመሪዎቹ አድሎአዊ ዘረኛ አስተዳደር ተማሮ እርስ በእርሱ በመታኮስ፤ የበርካታ የሰራዊት አባላት ሂዎት ሲቀጠፍ አይተናል፣ ሰምተናልም፤ ምንአልባት የእነ በረከት የቴሌቪዝን ካሜራ ይኼኛውን አላየው ይሆናል።

ሰራዊቱ ዛሬ በዘር መድሎ እየታሸ፣ ዘረኝነት ለስራ እድገትና ሹመት መመዘኛ በሆነበት፣ ስብእናው፣ ማንነቱ በህወሃት ካድሬዎች ተደፍሮ፣ ሙያው ተዋርዶ እና እርስበርስ ተከፋፍሎ ቀንን እየቆጠረ ባለበት ጊዜ፤ ይህንን ሰራዊት ኢትዮጵያዊ ውክልና ያለው አስመስለው፤ በክፉ ቀን ደራሽ አድረገው መቁጠራቸው ሞኝነት ነው።

ወያኔዎች መራራውን እውነት መራራም ቢሆን፤ በግልጽ የሚታይን፣  ያለውን እውነትና ነባራዊ ሁኔታ እስከመቼ በመካድ ራሳቸውን ሲያታልሉ ይኖራሉ? ሰራዊቱ በአሁኑ ሰአት በየግንባሩ እየከዳ ወደጎረቤት ሀገሮች በመሰደድ የተቃዋሚ ሃይሎችን እየተቀላቀለ ነው። ይህን የመከፋፈልና የመፍረስ ሃቅ ለመደበቅ የተቀነባበረ ትርኢት እናሳያችሁ ሲሉ ራሳቸውን ያታልላሉ።

በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ለዘረኛ መሪዎች የሀብት ማካበቻና የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ውድ ህይወቱን እንደ አልባሌ ነገር በሶማሊያ አደባባዮች እንደተፈጸመበት ሴራ ህይወቱን የሚገብርበት ቅንጣት ያህል ስሜት፣ ሁኔታ አሁን አይኖርም። በተለይም አበው የሰጡንን የታሪክ ማንነታችንንና ሃውልቶቻችንን በማፍረስ፣ አንድነታችንን በማናጋት ለበታተነን እና የአንድን ዘር የበላይነት መሰረት ላደረገ ስርአት፤ ሰራዊቱ ከቶ ክቡር  የሆነ ህይወቱን  አይለግስም።

ሰራዊቱ ከህዝብ አብራክ የወጣ ለህዝብ  በህዝብ የሆነ እንጅ በአሁኑ  ዘመን በገዛ ወገኑ ላይ ጥይት የሚያርከፈክፍበት ጊዜ ያለፈበት ለመሆኑ ከአረቡ አለም የጸደይ አቢዮት በተለይም ከግብጹ ህዝባዊ አቢዮት የህዝብ አሸናፊነት፣ ከመከላከያው ጠባቂነት ብዙ ትምህርት የቀሰመ ሠራዊት ነዉ።

እንግዲህ ይህን በዘርና በማንነቱ ከፋፍለው የያዙትን ሰራዊት፣ የእነሱን የከፋፍለህ ግዛ ጥቅም ያስከብርላቸው ዘንድ እየተመኙ ነገርግን ለፍርሃታቸው መደበቂያ አርቲስት ተብዪዎቹን በመጥራት “ኑ ጉልበታችንን እዩና ለህዝብ ንገሩ እኛ ብንናገር የሚሰማን የለም” ሲሉ መማጸናቸውን በቲቪ መስኮታቸው አይተናል። በርግጥ ነው አርቲስቶች የተከበረ ሙያቸውን ለዘር የፖለቲካ ስርአት፣ ህዝባዊ ውክልና ለሌለው አምባገነናዊ አገዛዝ መጠቀሚያ ማድረጋቸው በታሪክ ተጠያቂ ያስደርጋቸዋል።

ሰራዊቱ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት፣ አንድነቷ የተከበረባት፣ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት በሚደረገው ማናቸውም የህዝብ ትግል ከህዝብ ጎን በመቆም የአበውን የጀግንነት አርአያ በመከተል ለአምባገነኖች የስልጣን እድሜ ማራዘሚያና በደሙ ውስኪ ከሚራጩበት ለወያኔ አዛዦች መጠቀሚያ ከመሆን እምቢ ሊል የግድ ይላል። ከህዝብ አብራክ የወጣ የሀገር ልጅ ለሀገር አንድነት ህልውና፣ ለነጻነት ጮራ ትግል እንቅፋት መሆን የለበትም።

ሁሌም ህዝብ አሸናፊ ነው፤ ሙባረክ በአለም አለ የሚባል የጦር ሰራዊትና የቴክኖሎጅ ብዛት የነበረው አምባገነን መሪ ነበር፤ ጋዳፊ የመከላከያ ጡንቻቸውን በቴሌቪዥን መስኮቱ ደጋግመው ለአለም ሲያሳዩ ሲኮፈሱ ነበር፤ ከቶ የአንዱም የሰራዊት ሃይል የህዝብ ቁጣ ማእበልን ሊገታው፣ ሊያቆመው አልተቻላቸውም። ታዲያ የኛዎቹ ትንሽዪ አምባገነን ዘረኛ መሪዎች ምን ሸቷቸው ይሆን የሰራዊት ህብረ-ትርኢት ማሳየት የጀመሩት?

ህወሃት ሁሉን እንደሚያውቅ እና ጥንካሬውን በአዋጅ እንዲናገሩለት በመረጣቸው እንደራሴዎች ሲያስነግር፣ ነገርግን በአንጻሩ ባዶነቱንና የድንጋጤው መጠኑ ማየሉን ለህዝብ እያሳየ መሆኑን ልብ ያለው አልመሰለንም፤ ታዲያ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍርሃት አረንቋ በመውጣት የአየሩ ትርኢት ሳያስደነግጠው ትንሽም ትልቅም ቢሆን በራስ አነሳሽነት በየአካባቢው ተደራጅቶ ትግሉን በማገዝ ወያኔን በማስገደድ ወይም የማስወገድና የማፋፋም ሚና መጫዎት ይኖርብናል።

ሰራዊቱ የህዝብ ነጻነትና መብት ሲጠበቅ፤ የእርሱም የነጻነትና ዲሞክራሲያዊ እኩልነቱ እንደሚጠበቅ ተረድቶ ህዝባዊ የነጻነት ትግል ጎራን መቀላቀል ብልህነት ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!