0
Posted January 10, 2013 in News
 
 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ሂደት እየገፋ ያለው ለገዢው ፓርቲ ብቻ በተመቻቸ ሜዳ ነው!


ከ33ቱ የአዳማ ፔቴሽን ፈራሚ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ

 

በምርጫ አስፈፃሚው፣ ከምርጫ አስተዳደርና በምርጫው ሂደት ላይ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን በማንሣት ችግሮቹ ስለሚፈቱበት መንገድ የውይይት /ምክክር/ መድረክ እንዲመቻች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለመንግሥት አካላት ጥያቄአችንን ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማያሣምኑ ምክንያቶች በመስጠት ጥያቄዎቻችንን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን በቃል የገለፀልን ሲሆን ለመንግሥት ላቀረብነው ጥያቄ ምላሹን እየተጠባበቅን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የተጣለበትን የአገርና የሕዝብ ኃላፊነት ወደጐን በመግፋት ምርጫውን ሠላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ የመወዳደሪያ ሜዳውን ከማስተካከል ይልቅ የገዢው ፓርቲ ወገንተኝነቱንና ጉዳይ ፈፃሚነቱን ባረጋገጠበት አቋሙ በመግፋት ወደ ምርጫ እንቅስቃሴ መግባቱን በይፋ አውጇል፡፡

እኛ በያዝነው ሠላማዊ የትግል መሥመር በምርጫ የመሣተፍ /አለመሳተፍ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ያለመሆኑንና የሕዝብ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ጥያቄዎች ምላሽ የምንሰጥበት ብቸኛው የመንግሥት ሥልጣን መያዣ መሣሪያችን መሆኑን በተደጋጋሚ በግልጽ አስቀምጠናል፡፡ የአካባቢ ምርጫ ወደ ሕዝቡ ዘልቆ ለመድረስ የሚያስችል እንደመሆኑ ከአገር አቀፍ ምርጫ ያነሰ ትኩረትና ቦታ የምንሰጠው አይደለም፡፡ ይልቁንም ለምንፈልገው የሥርዓት ለውጥና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረቱ የሚጣለው በሕዝቡ ውስጥ ስለሆነ ለዚህ ምርጫ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ጠንክረን ለመንቀሳቀስ ዝግጅታችንን በተባበረና በተቀናጀ መንገድ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ባለንበት ነው የጋራ ጥያቄዎቻችንን ያቀረብነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ በኢህአዴግ እየተመራና እየታገዘ ከጊዜ ሰሌዳ በፊት በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ይቅደም በማለት 41 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዳማው ስብሰባ ላይ ላቀረብነው የቦርዱ ሰብሣቢ “የውይይት መድረክ ይዘጋጃል” በማለት የመለሱትን፣ እንዲሁም 33 በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ የምንታገል የፖለቲካ ፓርቲዎች ፔቲሽን ፈርመን ላቀረብነው የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ “ባትጠይቁንም ማድረግ ያለብን ነው” “. . .  ጉዳዩን ሣታጮሁት በትዕግሥት ጠብቁ” ማለታቸውን ክደው ከአዳማ በተመለሱ በ4ኛው ቀን አፀደቅን ባሉት የጊዜ ሰሌዳ ገፍተውበታል፡፡ በዚህ መሠረት ቦርዱ መዝግቤ የምሥክር ወረቀት ሰጠሁ ብሎ ከሚዘረዝራቸው 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 28ቱ ብቻ የምርጫ ምልክት በወሰዱት፣ የምልክት መምረጫ ጊዜ አልፏል /ተጠናቃል/፣ ከማለት አልፎ የሕዝብ ታዛቢዎ አስመርጬ የመራጮች ምዝገባ ጀምሬአለሁ፣ በቀጣይም በጊዜ ሰሌዳዬ መሠረት እቀጥላለሁ የሚል ዘመቻውን ተያይዞታል፡፡ በምርጫ ህጉ መሠረት በምርጫ ዘመን በፓርቲዎች የሚደረገው ቅስቀሳና በፓርቲዎች መካከል በመገናኛ ብዙኃን የሚካሄደውን የፖሊሲዎች አማራጭ አቀራረብ ቦርዱ በፍትሃዊነት የአየር ጊዜ ደልድሎ መምራት ሲገባው ራሱ አፀደቅሁ ካለው የጊዜ ሰሌዳ ውጪ በኢህአዴግና መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ /ክርክር/ ሲያደርጉ ማስቆም አልፈለገም፣ አልቻለም፡፡

በዚህ ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ነው ጥያቄዎቻችሁ የተመለሱ ናቸው . . .በማለት ወደ ምርጫ ማስፈጸም የገባው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የምርጫ መወዳደሪያው ሜዳ ተስተካክሏልና ያለአንዳች ጥያቄ በምርጫው ተሣትፋ ካልፈለጋችሁ ተውት የሚል የማንአለብኝነት ግልጽ መልዕክት ነው፡፡ ስለሆነም ለጉዳዩ ዋነኛና ቀዳሚ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ምርጫውን ለምትደግፉና ለምትከታተሉ የዓለም ማኅበረሰብ አባላት በድጋሚ የምናስተላልፈው ጥሪ ምርጫ ቦርድ በኢህአዴግ አይዞህ ባይነት በያዘው “ካፈርኩ አይመልሰኝ” አቋም መግፋቱ በጥያቄአችን መሠረት የምርጫ መወዳደሪያ ሜዳውን የሚያስተካክል ስላልሆነ በቀጣይ ተወያይተን የምናሳውቃችሁን የጋራ አቋም በንቃት እንድትጠብቁና ሂደቱን በትኩረት እንድትከታተሉ ነው፡፡

ቦርዱ 28 ፓርቲዎች ብቻ በተመዘገቡበትና ለጥያቄዎቻችን (ጥያቄዎቹ የ41 ፓርቲዎች መሆናቸውን በማጤን) መልስ ባልተሰጠበት ይልቁንም ችግሮቹ እየተባባሱ በመጡበት በምርጫው እቀጥልበታለሁ የሚለው አቋም ምርጫውን ተአማኒ አሣታፊ እና ተቀባይነት ያለው አያደርገውምና ውሣኔውን እንደገና በመመርመር ለአገራችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ለማድረግ አሁንም ጊዜው ያልመሸበት መሆኑን እንገልፃለን፡፡ ሌሎች አሁን በተያዘው የምርጫ ሂደት ውስጥ የገባችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረብናቸው ጥያቄዎችና ችግሮቹ የሃገርና የጋራ መሆናቸውን ተረድታችሁ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ዳግም አገራዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

በተባበረ ትግላችን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!

ታህሳስ 25/2005፣ አዲስ አበባ

በአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት የተሰራጨ

“Our voice may be small now, but together all of us can make a difference”