0
Posted January 5, 2013 in News
 
 

ውሸት ሲደጋገም…


ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ለ7ኛ ግዜ የሚያከብረዉን  የብሄር-ብሃረሰቦች ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕጽዋት በመትከል ትርጉም የለሹን ህገ-መንግስት አጠንክሮ እንዲጠብቅ የአምባገነኑ አገዛዝ ሃላፊዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ወያኔ የሚናገረዉና የሚሰራዉ እጅግ በጣም የሚቃረን ድርጅት መሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የኤኮኖሚ መዋቅሮች ብቻዉን ሙሉ በሙሉ እየተቆጣጠረ በአንድ በኩል ሀየማንነትና የእኩልነት ጥያቄዎች በህገ-መንግስቱ ምላሽ አግኝተዋል ይላል በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የተረጋገጠ እኩልነት ሊያሳየን የሚፈልገዉ ብሔር ብሔረሰበፐችን ሰብስቦ ዝፈኑ በማለት ነዉ::

ባለፉት 21 አመታት ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎቿ ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ እና በተለይም በገጠር የሚኖረው አርሶ አደር ገበሬ መሬቱ፣ ባህሉና ነጻነቱ እየተነጠቀ ለውጭ ባለጸጋዎች እየተቸበቸበ ባለበት ወቅትናት፤ በአገሪቱ የወልና የግል መብት ባልተከበረበት ሁኔታ ለይስሙላ ህዝብን በአደባባይ አስወጥቶ ማስጨፈር፣ ህዝብን ማታለልና በአገር መቀለድ ነው።

የብሄር-ብሄረሰቦች መብት የሚከበረው ወይም መከበር የሚጀመረው የግለሰብ ሁለንተናዊ መብት ሲከበርና ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ፤እኩልነትና ነፃነት ሲሰፍኑ ብቻ ነዉ። እነዚህ ሁሉ በሌሉበት፤ ግልሰቦች እየታሰሩ ግፍና ሰቆቃ እየተፈጸመባቸዉና ብሔር ብሔረሰቦች ደግሞ የፖለቲካ ስልጣን ተነፍገዉ የበይ ተመላካች ሆነዉ እየታየ ይሀ በየአመቱ ህዳር በመጣ ቁጥር የምናየዉ የብሔር ብሔረሰቦች  ሆይ ሆይታና ከበሮ ድለቃ የሚያስታውሰን የደርግ ስርዐት ሲያደርግ የነበረውን የአቢዎት በዓል አከባበር ነዉ።

በአንድ ወቅት የወያኔ  አምባገነኖች “የአክሱም ሐውልት ለአማራውና፣ ለወላይታው ምኑ ነው?” እያሉ በአገራችን ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ሲያፌዙ የነበሩት የወያኔ ዘረኞች ዛሬ ምን እየታያቸው ወይምእየሸተታቸው ይሆን ስለ ብሄር ብሄረሰብ የተቆረቆሩ የሚመስሉት የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም።

የጋምቤላ፣ የኦጋዴንና የታችኛው ኦሞ ወገኖቻችን መሬታቸውንና ባህላቸውን ተነጥቀው እየተሰደዱና እየተገደሉ ባሉበት አገር ኑናና ስለ ብሔር ብሄረሰቦች መብት መከበር ጨፍሩ መባሉ ከቶ አስተዛዛቢ ነው። በተለይም የአንድ ብሄር የበላይነት ስር ሰዶ በነገሰባት ኢትዮጵያ ዛሬ ለይስሙላ ለማስመሰል የሚደረግ ሩጫ መቆም ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ህዝብን በብሄር ብሄረሰብ ስም ጭፈራ ማታለል ይብቃ! የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ  የግለሰብና የወል መብቱ፤ነፃነቱና እኩልነቱሊከበርለት ይገባል። የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ እጦት በአለባት ሀገራችን፤ አምባገነኖች በህዝብ ስም የሚነግዱትን የማስመሰል ንግድ እና ውሸት በአስቸኳይ ተባብረን ልናስቆመው ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ በሚሆኑ ብሄር ብሄረሰቦች አገር መሆኗ  መሆኗ እየታወቀ በአንድ ብሄር የበላይነት ዙሪያ ያጠነጠነ ፌዴራሊዚም ፈጥሮ እራስን ፈላጭ ቆራጭ ሌሎችን ሌሎችን ተመልካች እንዳደረጉ መቀጠል በዛሬዉ መረጃ በነገሰበትና የለዉጥ ማዕበል አለማችንን ባጥለቀለቀበት ዘመን ከቶዉንም ሊታሰብ የማይችል የአምባገነኖች የቀን ህልም ነዉ። ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ባስቸኳይ የሚያስፈልጋቸዉ በአካባባያቸዉ እራሳቸዉን ካለምንም ተፅዕኖ ማስተዳደርና  በማዕከል ደግሞ የፖለቲካ  ስልጣንን ተጋርተዉ በእኩልነት መኖርን ነዉ፤ የፌዴራል ስርዐት አወቃቀርም የሚለዉ ይህንን እንጂ ተስብስቦ መዝፈንን አይደለም።

ለብዙ ዘመናት  ተከባብሮና ተሳስቦ  የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለመታደል ሆኖ ዛሬ አንተ አማራ፣ አሮሞ፣ ትግሬ፣ከንባታ… እየተባለ መታወቂያው የብሄር ማንነቱ ሆኖ አሳፋሪ ኑሮ እየኖረ ነው። ይህን ሀቅ ደብቆና ህዝብን አታሎ፣ አፍኖና ጨቁኖ አደባባይ ውጥታችሁ ስለብሄር መብት መከበር ከበሮ ደልቁ የሚለውን የወያኔ በማር የተለወሰ መርዝ የኢትዮጵያ ህዝብ በደንብ ሊረዳውና አምርሮ ሊታገለዉ ይገባል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔ ዘረኞች በአገሩና በማንነቱ ላይ የደቀነበትን የመከራ ቀንበርና ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ  በማስወገድ፤ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሆኖ አለም አቀፍ የሲቪክና የፖለቲካ መብቶች የተከበሩባትና ብሄር ብሄረሰበቿ በእኩልነት እጅ ለእጅ ተያይዘዘዉ የሚኖቱባትን ኢትዮጵያን መገንባት የሁላችንም ሀላፊነት ነዉ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!