0
Posted November 14, 2012 in News
 
 

ሰማዕታቶቻችንን ምንግዜም አንረሳቸዉም


“መስከረም ሲጠባ ህዳር ሲታጠን ያኔ አሳይሻለሁ አረማመዴን”

ይህንን ቆየት ያለ ስንኝ ማን እንደቋጠረዉ ባይታወቅም የሐምሌዉ ጨለማ፤ የነሐሴዉ ጭቃና ከሰኔ አስከ መስከረም የሚዘልቀዉ የእርሻ ላይ ዉሎ ከሌላ ማህበራዊ ኑሮ የነጠለዉ የኢትዮጵያ ገበሬ ለሚወዳት ፍቅረኛዉ የተቃኘዉ ቅኔ ይመስላል። ሰኔ በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ገበሬዉ መስከረም ላይ የሰቀለዉን ሞፈርና ቀንበር መልሶ የሚያወርድበት ወር ሲሆን መስከረም ደግሞ አምስት ወር ሙሉ የጨበጠዉን ሞፈርና እርፍ መልሶ የሚሰቅልበት ወር ነዉ።

አዎ… ሰኔ የክረምቱ መግቢያ መስከረም ደግሞ የአዴይ አበባ መፍኪያ ግዜ ነዉና መስከረምና ሰኔ ለኢትዮጵያ ገበሬ ብዙ የሚሉት ነገር አለ። ጠላትንና የአገር ልጅን ባዳና ወገንን የማይለዩትን የወያኔ አግዓዚን መትረየሶች ለሚያስታዉስ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ሰኔ 1997ና ጥቅምት 1998 ቢያጥቡት በማይጠራ ቢፍቁት በማይደበዝዝ የጽልመት ትዝታ የተሞሉ ወራት ናቸዉ። በየአመቱ ሰኔና ህዳር በመጡ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ ገላ እንደገተገፋ አጥር ይፈርሳል፤ ልቡ ነዳጅ እንደጨረሰ መኪና ቀጥ ይላል። በ1998 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ህዳር ሲታጠን ለማሽተት ወይም ህዳር ሚካኤልን ለማክበር አልታደለም። በዘረኞች መትረየስ ልጆቹን የተቀማዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በ1998ቱ ህዳር የታጠነዉ እሱ እራሱ ባጨሰዉ ዕጣን ሳይሆን በወያኔ አግአዚ የባሩድ ሽታ ነበር።

ዘመናዊቷ የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በልጆቻቸዉ ደም ደጋግመዉ ከታጠቡ የአፍሪካ መዲናዎች አንዷ ናት። አዲስ አበባ በ126 አመት ታሪኳ ዉስጥ ብዙ እሴይ የሚያሰኙ ብሔራዊ ድሎችን እንዳስመዘገበች ሁሉ ብዙ አንገት የሚያስደፉ ህዝባዊ እልቂቶችንም አስመዝግባለች። በእርግጥም አዲስ አበባ ክፉዉንም ደጉንም አስተናግዳለች። ሆኖም እቺ ታሪካዊ ከተማ ማርሻል ግራዚያኒ፤ ከኦሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያምና ሹምባሽ መለስ ዜናዊ የፈጸሙትን አይነት እልቂት በታሪካ አይታም ሰምታም አታዉቅም።  እነዚህን ሦስት ፋሺስቶች በንጹህ ኢትዮጵያዉያን ላይ የፈጸሙት ወንጀል የኢትዮጵያ ታሪክ ዝንተአለም የሚዘክረዉ የታሪክ ጠባሳ ነዉ።

ለመኪናና ለእግረኛ ደምቀዉ የተሰሩትን የፒያሳ፡ የካዛንቺስ፤ የመርካቶ፤ የአራት ኪሎና የስድስት ኪሎ መንገዶች ግራዚያኒ  በኢትዮጵያዉያን  ደም ሲያጥበዉ አዲስ አበባ ገና የ54 አመት ጎልማሳ ነበረች። ግራዚያኒ ይህንን አሰቃቂ እልቂት ከፈጸመ ከ41 አመታት በሁዋላ በ1969 ዓም እነዚሁ የአዲስ አበባ መንገዶች ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም ብለዉ የጠየቁ ወጣቶች ደም እንደ ዉሀ ፈሰሰባቸዉ። ይህ ከሆነ ከ14 አመት በኋላ  ወያኔ ደርግን አሸንፎ  አዲስ አበባም የሠላምና የእድገት እንጂ የእልቂት ከተማ እንደማትሆን ቃል ተገብቶ ነበር። ሆኖም ደም እያፈሰሰ ስልጣን ላይ የወጣ ስልጣን ላይ መቆየት የሚችለዉ ደም እያፈሰሰ ነዉና በ1997 ዓም እነዚያ ደም የለመዱት የአዲስ አበባ መንገዶች በሽብሬ ደሳለኝ፤ በየሱፍ አብደላ፤ በነቢዩ አለማየሁ፤በፈቃዱ ነጋሽ፤ በአብርሃም ይልማ፤ በዙልፋ ሱሩር፤ በትንሳኤ ዘገየ፤ በሀብታሙ ቶላ፤በቢንያም ደገፋ፤በቃሲም አሊ፤ በቴዎድሮስ ግደይ፤ በረጋሳ ፈይሳና በሌሎችም ቁጥራቸዉ በበዛ ንጹህ ኢትዮጵያዉያን አስከሬን ተሸፈኑ። ለወትሮዉ የጥቅምት አበባ ሽታ የሚያዉዳት አዲስ አበባ በልጆቿ ደም ሽታ ታወደች። ከክረምቱ ብርድና ጨለማ የተገላገለዉን የአዲስ አበባ ነዋሪ ቤት የሞት ጽላሎት ሞላዉ። ኢትዮጵጵያ በሀዘን ተዋጠች። የኢትዮጵያ ህዝብ በንጹህ ልጆቹ ሞት ወያኔና አግዓዚ ደግሞ ያሰቡትን ያክል ባለመግደላቸዉ ሁለቱም አዘኑ።

ወያኔና አግዓዚ ወደዱም ጠሉ፤ፈለጉም አልፈለጉ የኢትዮጵያ ህዘብ እነሱ በፈጠሩት ዘረኛ ስርዐት ከርሰ መቃብር ላይ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባቱ አይቀርም። ሆኖም “ዲሞክራሲ” የምንለዉ ጽንሰ ሀሳብ ከምርጫ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ በተካሄደ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዘብ የ1997ቱን ምርጫ ምን ግዜም ቢሆን ማስታወሱ አይቀርም። በተለይ ሰኔና ጥቅምት በመጡ ቁጥር ልጆቻቸዉን ያጡ ወላጆችና ወላጆቻቸዉን በአግዓዚ ጥይት የተነጠቁ ወጣቶች ልብ በኃዘን ይሞላል። የ1997ቱ ምርጫ  የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ሺ አመታት ታሪኩ ዉስጥ ዲሞክራሲን ለመጀመሪያ ግዜ ያጣጣመበትና ነፃነትና ዲሞክራሲ የሚያስከፍሉትን መስዋዕትነት ተረድቶ ዉድ ልጆቹን ለመብቱና ለነፃነቱ የገበረበት ታሪካዊ  ምርጫ ነዉ።

ምርጫ 1997ትን ተከትሎ ወያኔ ሰኔና ጥቅምት ላይ የጨፈጨፋቸዉ ዜጎቻችን ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የሚያንገበግበንና የሚቆጨን የንጸህ ዜጎቻችን ሞት ብቻ ነዉ ብለን የምናስብ ካለን እጅግ በጣም ተሳስተናል። የ1997ቱና የ198ቱ ግድያ “እኛና” “እነሱ” በሚል ጥላቻ፤ቂም በቀልና ዘረኝነት ላይ የተመሰረተ  ግድያ ነዉ። ይህ ግድያ ከንጉስ ሄሮድስ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ህፃናት ወላጆቻቸዉ ፊት የተገደሉበት አሰቃቂ ግድያ ነዉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ ግድያ በ1700 አመታት የክርስትና ታሪካችን ዉስጥ ለመጀመሪያ ግዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርሰቲያን ባሩድ ከሚተፉ መትረየሶች ለማምለጥ የተጠጓትን ልጆቿን አላዉቃችሁም ብላ በሮቿን የዘጋችበት  የጨለማዉ ታሪካችን አካል ነዉ።

ዛሬ እኛ ኢትዮጵያዉያን የሰማዕታት ቀን ብለን የምንጠራዉን የዬካቲት 1928ቱን እልቂት፤ የ1969ኙን የኮሎኔል መንግስቱ እልቂትና የህዳር 1998ቱን እልቂት የሚለያያቸዉ ነገር ቢኖር የመጀመሪያዉ በነጭ ፋሺስቶች ሁለተኛዉና ሦስተኛዉ ደግሞ አገር በቀል በሆኑ ጥቁር ፋሺስቶች መፈጸማቸዉ ብቻ ነዉ። ፋሺስት ግራዚያኒ ከ30ሺ በላይ ኢትዮጵያዉያንን በእንድ ጀምበር ቢጨርስም የእነዚያ ጀግኖች ኢትዮጵያዉያዉያን ደም በከንቱ ፈስሶ አልቀረም። በመጋቢት ወር 1933 ዓም ግራዚያኒና አግበስብሶት የመጣዉ ወራሪ ጦሩ በጀግኖች አባቶቻችን ተሸንፎና ዉርደት ተከናንቦ ኢትዮጵያን ለቅቆ ወጥቷል። የማይነካና የማይደፈር ይመስለን የነበረዉ ኮሎኔል መንግስቱም ለእግሩ ጫማ በሌላዉ ጦር ተሸንፎ ከአገር ሸሽቶ ወጥቷል። የንጹህ ኢትዮጵያዉያንን ደም አፍስሶ ዛሬም ድረስ ዜጎችን እያሰረ፤እየደበደበ፤እየገደለና ከአገር እንዲሰደዱ እያደረገ የእጁን ሳያገኝ ተዝናንቶ የሚኖር ኃይል ቢኖር ወያኔ ብቻ ነዉ። አዎ! ዛሬ ኢትዮጵያ የምትመራዉ ልባቸዉ በጥላቻና በተሞላና እጃቸዉ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ደም በተጨማለቀዉ ጨካኝ ዘረኞች ነዉ።

እኛ ኢትዮጵያዉያን ዶጋሌ፤ አድዋና፤ ማይጮዉ ላይ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖቻችንን ለዘለአለም እንደምናስታዉሳቸዉ ሁሉ ወያኔ የጨፈጨፋቸዉን ሰማዕቶቻችንንም ሁሌ እናስታዉሳቸዋለን። እነ ሽብሬ ደሳለኝ፤ ነበዩ አለማየሁና ቃሲም አሊ ግን ከእኛ የሚፈልጉት እንድናስታዉሳቸዉ ብቻ ሳይሆን እነሱ የተሰዉለትን አላማ ከግቡ እንድናደርስ ነዉ። አዎ! በአስራ ሁለትና በአስራ ስድስት አመት ለጋ ዕድሜያቸዉ ግንባራቸዉን ለአግዓዚ ጥይት የሰጡት የነቢዩ አለማየሁና የቢንያም ደገፋ ሞት ለእኛ ህይወት የሚሆነዉ የወያኔን ዘረኛ ስርአት ደምስሰን ኢትዮጵያ ዉስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት መገንባት ከቻልን ብቻ ነዉ፤ አነነቢዩም ወደታች ዝቅ ብለዉ በተመለከቱን ቁጥር ለካስ አልሞትንም ብለዉ የሚዝናኑት የእነሱ ሞት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሆኖ ሲያዩት ብቻ ነዉ።ስለሆነም ዛሬ ሰማዕታቶቻችንን በምናስታዉስበት ወቅት ትልቁ ትኩረታችን ወደኋላ የማንመልሰዉ የወገኖቻችን ሞት ሳይሆን ፊት ለፊታችን ላይ ያለዉና በጅምር የቀረዉ እነሱ የቆሙለት አላማ ነዉ። ዛሬ እነነቢዩ  ከእኛ የሚጠብቁት ኃዘን ሳይሆን  እኛም እንደነሱ ነፃነቴን ወይም ሞቴን ብለን የመጨረሻዉ መስመር ላይ “ዘረኝነት በቃ” ብለን እንድንቆም ነዉ።