1
Posted September 30, 2012 in Amharic news
 
 

‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመሰባሰብ ትልቅ ጉልበት መፍጠር አለባቸው›› አንዱዓለም አራጌ (ከእስር ቤት)


የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራሮች መስከረም 17 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በሽብርተኝነት ስም ታስሮ የሚገኘውንና እና የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆነውን አቶ አንዱዓለም አራጌን ቃሊቲ በመገኘት ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ በአካል በመገኘትና ለመጠየት በቅቷል፡፡ አመራሩ በተጨማሪም የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆነውንና ቂሊንጦ ታስሮ የሚኘውን አቶ ናትናኤል መኮንንም እንደጠየቀ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ገልጿል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አያይዞ እንደገለጠው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካላት፣ አባላትና ደጋፊዎች ባለፈው አንድ አመት አንዱዓለምንና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ለመጠየቅ ከተመዘገቡ ጥቂት ቤተሰቦች በስተቀር መጠየቅ ሳይቻል ቀርቷል፡፡
በተደጋጋሚ በተደረገው ሙከራ ተስፋ ባለመቁረጥና ሀገ መንግሥታዊ መብትን በመጠቀም የመስቀል በዓል ቀን የአንድነት ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ አባላትና ከብሔራዊ ም/ቤት አባላት የተውጣጡ ሰዎች አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ ናትናኤል መኮንን ለመጠየቅ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ከከፍተኛ አመራሮች መካከል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ አቶ ሙላት ጣሰው፣ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ሽመልስ ሀብቴ፣ አቶ ደምሴ መንግሥቱና ሌሎችም የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትና የፓርቲው የምክር ቤት ሰብሳቢና ፀሐፊም ተገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ15 በላይ የሚሆኑ ጠያቂዎች ከጠዋቱ 2፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ ቃሊቲ ከተሰባሰቡ በኋላ እንደሌሎች ጠያቂዎች መግባት ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል፡፡ የእለቱ ተረኛ ጠባቂዎች ስልክ ከተደዋወሉ በኋላ ‹‹በ6 ሰዓት ኑ ትገባላችሁ›› በማለት መልሰዋቸዋል፡፡ የአንድነት ልዑካንም ተስፋ በማድረግ በጽናት እዚያው የጠበቁ ሲሆን 6 ሰዓት እስከሚሆን በዶ/ር ነገሶ የተመራ ቡድን ቅሊንጦ ወደሚገኘው ናትናኤል መኮንን ጋር በማምራት ከብዙ ንትርክ በኋላ ጠይቀው መለሳቸውን የህዝብ ግንኙነት አስታውቆአል፡፡
በተባለው ሰዓት መሰረት ወደ እስር ቤቱ የደረሱት አመራሮች ለመግባት ቢሞክሩም ‹‹ከተመዘገቡ ሰዎች ውጭ መግባት አይፈቀድም›› በማለት ተከልክለዋል፡፡ የያዙት ምግብ መግባት ቢችልም የመልካም ምኞት መግለጫ የሆኑ ፖስትካርዶች መልእክታቸው እየተነበበ አብዛኞቹ እንዳይገቡ ተደርገዋል፡፡ አብዛኞች የተመለሱት የሚያጽናኑ ጠንካራ ቃላትን የያዙና አንዱዓለምን እንደጀግና የሚቆጥሩ መልእክቶች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንዳይገቡ የተከለከሉ የአመራር አባላት የማረሚያ ቤቱን አስተዳዳሪዎች በማግኘት ‹‹ለምን ህገ መንግሥታዊ መብታችን አይከበርም? ታሳሪዎችን የመጠየቅ መብትስ ለምን ይገፈፋል?›› ብለው በጽናት በመጠየቅ በመጨረሻ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው አንዱዓለም አራጌን ከአንድ ዓመት በኋላ ፊት ለፊት አግኝተው ለመጋገር መቻላቸውን የህዝብ ግንኙነት መረጃ ይጠቁማል፡፡
የፓርቲው አመራሮች ዙሪያውን በከበቡ ጠባቂዎች መካከልም ቢሆን አንዳንድ ቁምነገሮችን ለመጫወት ችለዋል፡፡ ከፍተኛ የመንፈስ ጥንካሬና የሞራል ልዕልና የሚታይበት አንዱዓለም ለከፍተኛ አመራሩ ‹‹በማንም ላይ ክፉ ነገር ለማድረግ አስቦ እንደማያውቅና ፍፁም ነፃነት እንደሚሰማው›› የተናገረ ሲሆን የአንድነት አመራሮችም ከጎኑ በመሆን ከዚህ በፊት እኔ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንደማልፈልግ ገልጨ ፓርቲው ግን ወደ ፍርድ ቤት በሄድና መከራከሩ ቢያንስ ለታሪክ እንኩዋን ይጠቅማል በማለት መሄዱ አስፈላጊ መሆኑን በማመኑና እኔንም በማሳመን እንድከራከር በማድረጉ ጥሩ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ አሁንም ፓርቲዬ ይግባኝ እንዲጠየቅና ክርክርሩ እንዲቀልጥ በስራ አስፈፃሚው በመወሰኑ እኔም ይኸው ይግባኝ እንዲጀመር ተስማምቻለሁ፡፡ በአጠቃላይም ለፓርቲዬ አመራር ከፍተኛ ምስጋናም አቀርባለሁ ብሎአል፡፡
አንዱዓለም ‹‹ትግሉን አጠናክሮ ከመቀጠል ውጭ ምርጫ እንደሌለና የተበታተኑ ተቃዋሚዎች በመሰባሰብ ጠንካራ ኃይል ቢፈጥሩ እንደሚጠቅም ተናግሮ የእሱም አላማ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር እንጅ ሌላ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡››

አመራሩም ምንጊዜም ከጎኑ እንደሆኑና ትግሉንም ግቡን እስከሚመታ አጠንክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጦለታል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ እንደተናገሩት ‹‹እንድንገባ የተደረገው አስበውበት ከሆነ ጥሩ ነው፤ ወደፊትም እንዲፈቱ መጠየቃችንና ከጎናቸው መሆናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ግን እንድንገባ የተደረገው በድንገት ነው ወይስ ታሶቦበት? የሚለውን ለመመለስ በተከታታይ በመጠየቅ ማረጋገጥ ይኖርብናል›› ብለዋል፡፡