1
Posted September 6, 2012 in News
 
 

በኦስሎ በታላቅ ሕዝባዊ ስብስባ ሰማእታት ታስበው ዋሉ


በዳዊት ዋስይሁን /በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የሕዝብ ግንኙነት/

ሰብቴምበር 2፣ 2012 በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ የኖርዌይ ክፍል የተዘጋጀ፣ በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ባለፈው 21 መራራ የግዞት አመት በስርአቱ ቁንጮ አመራር ስጭነት በብዙ ወገኖቻችን ላይ ስቃይ፣ መከራ፣ እንግልት፣ እስራት፣ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸውን ዜጎች በማስብ የሰላማዊ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በዚህ ሰልፍ ላይ ሰፊ ቁጥር ያለው የማህበረሰባችን አባላት ተገኝቶ ፕሮግራሙን የተሳካና የደመቀ እንዲሆን አድርገውታል፣

በእለቱም ተስብሳቢው ለ21 አመት ለደረሰው የማህበረሰብና የሃገር ክስረትና ውድመት ተጠያቂው ስርአቱን ሲያዋቅርና ሲመራ የነበረው መለስ ዜናዊ እንደሆነ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች በአጽኖ ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ የከተማዋ እንብርት በሆነው አደባባይ ላይ ከቀኑ 14፡00 እስከ 16፡00 የተከናወነ ሲሆን በእለቱም በአለፉት 21 አመታት በፈላጭ ቆራጩና አምባገነኑ ስርአት ሰለባ ለሆኑ የአገራችን ዜጎች በአቶ አርጋው የእቆብ አማካኝነት የህሊና ጸሎት በማድረግ ፕሮግራሙ ሲጀመር፣ በመቀጠልም የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ማተቤ መለስ የሰላማዊ ሰልፉን ይዘት ሲገልጹ ለዘመናት እንደጭድና ጭቃ ተዋህዶ የኖረውን የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሃይማኖት ከፋፍሎ ሲያስተራርደው የኖረው አረመኔው መለስ ዜናዌ ዛሪ አምርሮ ይጠላትና ለጥፋቷም ቀን እረፍተ ሌት እንቅልፈ አጥቶ ለ21 አመታት የሰራባትን የኢትዮጵያን አፈር ይቀምሳል እንኳን ደስ ያለን!! በማለት ለተሰብሳቢው ከገለጹ በኋላ ሲያጠቃልሉ መለስ ሞተማለት የገነባው ስራአት ፈረሰ ማለት አይደለም ስለዚህ ማተኮር ያለብን በቀጣይ ምን እናድርግ በሚለው ላይ ነው አገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለችው እኛ ከፍ ሲል በዘር ሲወርድ በድርጅት አጥር እየተከለልን በመነታረክ ለአለፉት 21 አመታት የተፈጸሙት ግፎች ቀጣይ እንዲሆኑ መፍቀድ የለብንም ካሁን ወዲያ መለስ የቀየሰልንን የመከፋፈል አባዜ ዛሬ ከእሱ ጋር በመቅበር ተባብረን አገራችንን ከውድቀት ህዝባችንን ከውረደት የምናድንበት ቀኑ ዛሬ ስአቱም አሁን ነው። በማለት መልክት ካስተላለፉ በኋላ ለአቶ ዳዊት መኮንን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሊቀመንበር መድረኩን ለቀዋል።

ሊቀመንበሩም በመጀመሪያ ለኖርዌጅያን ማህበረሰብ በቋንቋቸው የሰልፉን ዓላማ ካብራሩ በኋሏ ለኢትዮጵያውያን ድግሞ በአማርኛ ዛሬ ኢትዮጵያ አንድ ጀግና ሳይሆን አንድ ጨካኝ መሬ ቀብራለች ዛሬ ኢትዮጰያ የዘርና የጎሳ ክፍፍል ማሃነዲስ ቀብራለች ዛሬ ኢትዮጵያ የዳኞችን ዳኛ አንባገነን ቀብራለች እንግዴህ ከእኛ ምን ይጠቃል? ላለፉት 21 አመታት ያልተጎዳና ያልተጠቃ የህብረተሰባችን ክፍል የለም ከጨቅላ ህጻናት ጀምፎ እስከ አዛውንትና አሮጊቶች ከሃይማኖት ተከታይ እስከ ሃይማኖት አልባው ከተማረው እስካልተማረው በጠቅላላው ማህበረሰባችን ተገድሏል፣ ተሰቃይቷል፣ ታስሯል፣ ተጨፍጭፏል ይህ ይበቃናል ከአሁን በኋላ ግፍን የምንሸከምበት ጉልበትና አቅም የለንም አሁን ስርአቱ ወደ ከርሰመቃብር ሊወርድ እየተንገዳገደ ነው ያለው በመሆኑም ይህ የበስበሰ ስርአት እና ያለቀለትን አገዛዝ በቁጭትና በአንድነት በመነሳት ገፍቶ በመጣል ታሪክ የጣለብንን አደራ መወጣት የያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው በማለት ከአደራ ጭምር መልክት አስተላልፈዋል።

በመቀጠል የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን በመወከል አቶ ሞላ አላምነሀ ባደርጉት ንግግር ሁለት ቁምነግሮች ላይ ረገጥ አድርገው ያሰምሩበት ሲሆን አንደኛው ያለፈው 21 አመት የተሰውት ሰማእታት ሁሌም የምንዘክራቸውና የምናከብራቸው ሲሆን በቀጣይም ይህ አምባገነን መሪ ዛሬ ወደ ከርሰ መቃብር ሲወርድ በህዝብ መካከል የተዘራ ጥላቻና አለመተማመን ከስርአቱ ቁንጮ ጋር መቀበር እንዳለበት፤ ሁለተኛው እርሱ ተክሎት የሄደውን የተበላሸ ስርአት የመለወጥ አላፊለት የሁላችንም እንደሆነ በአንክሮ ገልጸዋል።

በቀጣይ ዶ\ር ሙሉአለም አዳም ለተሰበሰበው ህዝብ ስለሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ካብራሩ በኋላ ለመታገል መደራጀት ዋናውና ቁንፉ መሆኑን በመግለጽ ሁላችንም መደራጀት እንዳለብን ማሳሰቢያዊ ምክር በመሰጠት ወያኔዎች ፈሪዎች ናቸው የፈሪ ዱላው ብዙነውና ወደፊት የከፋ ነገር እንደሚክስት እገምታለሁ ስለዚህ ለውጥ ስለተመኘነው ብቻ የሚመጣ ሳይሆን በቆረጡ በተደራጁና መስዋእትነትን ለመክፈል በወሰኑ ታጋዮች የሚገኝ ውጤት ነው በማለት ንግግራቸውን ጨርሰዋል።

ከዚያም የቀድሞ የህውሃት መስራችንና ታጋይ የነበሩት አቶ ግደይ ዘርአጽዮን መለስ ምን አይነት የተበላሸ ስርአት ሲመራ እንደነበር እና በተለይ በአገሪቷ ለተከሰቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ የማህበራዊ ችግሮች ዋናውና ተጠያቂው እርሱ መሆኑን ካብራሩ ብኹአላ በየፈርጁ አስመዝግቤያቸዋለሁ የሚላቸውን የኢኮኖሚ እድገቶች ሚዛን ያልደፋና በውሽት ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ የተቀነባበሩ እንደሆነ በማሰረጃ በማስደገፍ ሲያብራሩ ለቀጣይ ስራና ትግልም የግድ ተባብሮ መስራት አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ በአንክሮ ገልጸዋል።

ሌላው ተናጋሪ በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ፋሲል አለባቸው ባሰሙት ንግግር እኔ የምናገረው እንደ ፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን የማህበራችን መተዳደሪያ ደንብ በሀገርና በወገን ላይ ለሚፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶች መወገድ የድርሻችንን መወጣት እንዳለብን ስለሚያዝ ነው በማለት 21 አመታት መለስ ዜናዌ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸመውን በደል በሰፋት ገልጸዋል።

በመቀጠል አቶ አምሳል ካሴ ሀገራችንን ወደብ አልባ የሆነችው፣ ዙሪያዋን እየተቆረጠች ለጎረቤት ሀገር የታደለችው፣ ሴት እህቶቻችን ወደአረብ ሀገር መሸጥ የተጀመረው፣ ከኑሮ ውድነት የተነሳ ጉርሻ በአደባባይ መሸጥ የተጀመረው ወ.ዘ.ተ. በመለስ ዜናዌ ዘመነ ሰልጣን ስለሆነ የእሱ ሞት ከምንም በላይ አስደስቶናል ብለዋል።

እንዲሁም አቶ እንግዳ ታደሰ ባህላችን እና ሃይማኖታችን የተደፈረበት ድንበራችን ለባእድ ተቆርሶ የተሰጠበት በኢንቨስትመንት ስም ደሃ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው የተፈናቀሉበት ንጹሃን ዜጎች የተፈጁበት ወገኖቻችን በገፍ ወደ ስደት የተዳረጉበት መከራና እንግልት የበዛበት ያለፉት ሃያ አንድ አመታት በታሪካችን ልንረሳው የማንችል ጥቁር ጥላሸት ጥሎበት ያለፈ ነው ሲሉ ለመጪው ትውልድ እንደዚህ አይነት ክስተት እንዳይደገም  ነጻና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ተጠየቂነት የሰፈነበት ስርአት እንዲፈጠር ጠንክረን መስራትና መታገል እንዳለብን አስረግጠው አብራርተዋል።

ከዚያም የምንኮራባትና እህታችን የሆነች ሜርሲ ከልብ የፈለቀ አገራዊ ስሜቷን የተለያዩ ቀስቃሽ ንግግሮችን በማድረግና ተወዳጅ የአገርን ፍቅር የሚገልጹ ዜማዎች በማስዘመር ለሰማእታት ያላትን ፍቅርና አክብሮት ገልጻለች በማያያዝም በአቶ ልዑል መኮንን ታዳሚውን ያስደመመ ንግግር ሲያደርጉ አቶ መለስ ለኢነርጂ ፎር ኦል ስብሰባ ባለፈው አመት እዚህ ኦስሎ የመጡ ግዜ የአንድ ትልቅ የታወቀ የኖርዌይ ጋዜጣ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሚሰጡበት ውጭ ስላለው ተቃውሞ ሲጠይቃቸው ”ይህ ተቃውሞ እንደዚህ እንደምታዩት ደመና ብን በሎ ይጠፋል ” ማለታቸውን አስታውሶ እኛ አለን ገናም እንኖራለን እሳቸው ግን ብን ብለው ጠፉ ገናም ኢትዮጵያን የተዳፈሩ ብን ብለው ይጠፋሉ በማለት ሲያብራሩ በመያያዝም ወንድምህ ቃየል የት ነው የሚል የእንግሊዝኛ ግጥም አሰምተዋል።

በማስከተል አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ቀስቃሽና ወቅታዊ የአገራችንን ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ግጥም አቅርበዋል በመጨረሻም በዲሞክራሲያዌ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበርና የሰልፍ አዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ በሆኑት በአቶ ማተቤ መለሰ በምስጋና የታጀበ የመዝጊያ ንግግር ከቀኑ14፤00 ስአት የተጀመረው ህዝባዊ ሰብሰባ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከቀኑ 16፡00 ስአት ተጠናቋል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ኦስሎ ኖርዌይ ሰፕቴምበር 05፣ 2012