0
Posted June 15, 2015 in Amharic news
 
 

ለእውነት እንዳንታገል አዚም የሆነብን ምንድር ነው? ይበልጣል ከኖርዌይ


ስለ እውነት በተግባር እንጂ በቃል ደረጃ ብዙ ማለት ከባድ ቢሆንም ብዙዎች ብዙ ጽፈዋል ተናግረዋል።እውነት ማለት ያዩትን፣ የሰሙትን፣ የሚያውቁትን፣ የተረዱትን፣ የሆኑትን እና የሚያምኑበትን ነገርሳይጨምሩ ሳይቀንሱ በግልም ሆነ በአደባባይ በይፋመናገርና መመስከር መቻል እንደሆነ የዘርፉ ሙህራን ያስረዳሉ።  በሌላ መልኩ ደግሞያላዩትን፣የማያውቁትን፣ ያልሰሙትን፣ ያልሆነን ነገር ሳያረጋግጡ እና የማያምኑበትን ጉዳይ አለመናገር ማለትእንደሆነም አክለው ያስረዳሉ፡፡ በአጭሩ እውነት የሀሰት ተቃራኒ ነው። እውነት ለመናገር፣ ስለ እውነት ለመመስከር በመጀመርያ ሀሰትን መቃወም ይኖርብናል። ስለ እውነት ለመናገር ያልቆሸሸ ንጹህ ሕሊና ሊኖረን ይገባል። ንጹህ ሕሊና እውነተኛ ዳኛ ነውና። ያልተበረዘ፣ያልቆሸሸ እና ንጽህ ሕሊና ሀሰትን የማስተናገድ ባህሪ የለውም።

ሀቀኝነት፣ ታማኝነት፣ እርግጠኛነት፣ ትክክለኛነት፣ ተጠያቂነትን መቀበል እና ሀላፊነትን መወጣት የእውነት መገለጫ ባህሪያት ናቸው። በሌላ አነጋገር እውነት ማለት ጽድቅን ማድረግ፣ መልካም ሥነ ምግባርን መላበስ እና ለነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ግንባታ መታገል ማለት ነው። እውነት ማለት ሀገር፣ ታሪክ፣ ባህል እና ማንነት ነው። እውነት አድሎ የማይታይበት፣ ርህራሄና ቸርነት በተሞላበት ለሰው ልጅ ሁሉ መልካም ነገር እንዲያገኝ መመኘትና በጎ ተግባራትን ማከናወን ነው። እውነት የሰው ልጅ ዘላቂ ሰላም እና የተረጋጋ ህይወት እንዲያገኝ ከፍተኛ አስትዋጾ ያደርጋል።
ቀደምት አባቶቻችን  ስለእውነት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን በሰማዕትነት አሳልፈው ሰጠዋል፤ ብዙ መከራና ስቃይ ተቀብለዋል። ለእውነት ሲሉ ከጊዜያዊ ጥቅም ታቅበዋል። ዛሬም ለእውነት ሲሉ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙ እውነተኛ የእውነት ምስክሮች በብዙ ስቃይና መከራ ውስጥ ይገኛሉ። በብዙ ውጣ ውረድ እውነትን መናገር እጅግ መልካምና ልብን የሚያስደስት ቢሆንም እውነትን የሚወዷትን ያህል የሚፈሯትና ከቻሉም በሀሰት ለውጠው ለማጥፋት የሚመኙ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ ጥቅምና ስልጣን ፈላጊዎች እንዲሁም አምባገነን መሪዎች በዋናነት ለእውነት መጥፋት ዋነኛ ተዋናኞች ናቸው፡፡
አምባገነን መሪዎች እውነትን መከተልም ሆነ መስማት አይፈልጉም። መነሻቸውና ግብራቸው ሀሰት ስለሆነ እውነትን ፈጽመው አያውቋትም። እርግጥ ነው እውነት ለእነሱ ጠላት ናት፤ ታጠፋቸዋለች። እነርሱ የሀገር መጥፋት፣ የታሪክ መዛባት፣ የህዝብ ሰላምና ደህንነት አያስጨንቃቸውም። ለሥልጣን ማራዘሚያ ሀገር ይሸጣሉ፣ ህዝብን ይጨቁናሉ፣ ይገድላሉም።

በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ማውራትና መስበክ ወንጀል ከሆነ ዘመናትን አስቆጥሯል። በዚህ ዙርያም ለምን እና እንዴት ብለው የሚጠይቁ ዜጎች እጣ ፈንታቸው እስር፣ እንግልትና ሞት ሆኗል።በኢትዮጵያም ያለው ይህ እውነትን የሚፈራ እና ከእውነት ፈጽሞ የተጣላ የህወሓት አገዛዝ ለሀቅ፣ ለእውነት የቆሙትንና ሕዝብ እውነትን ያውቅ ዘንድ ያለመታከት እየሰሩ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፣ ጦማርያንን፣ የፖለቲካ መሪዎችን እና ንጹሃን ዜጎችን ማሳደድናማሰር ቀጥሎበታል፡፡ በአጠቃላይ ለነጻነት፣ፍትህና ዲሞክራሲ የሚታገሉ ውድ ኢትዮጵያውያንን  ወያኔ ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ ወደ ግዞት እንዲወረወሩ ማድረግ፣ መግደልና ማሰቃየት የሥርዓቱ ተቀዳሚ ተግባር አድርጎታል። ወያኔዎች ሰባዊነት የሚባል በውስጣቸው ቅንጣት ስለሌላቸው በነጻነት ታጋይ ኢትዮጵያውያን ላይ የአካልና የሥነ ልቦና አሰቃቂ እና ኢ_ሰባዊ ድርጊት ካለ ምንም ርህራሄ ይፈጽማሉ፤ ዛሬም በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።

የወያኔ ፈላጭ ቆራጭ፣ ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰው ግፍና ሰቆቃ ከመብዛቱ የተነሳ ለእውነት እንዳንቆም እንቅፋት ሆኖብናል። ብዙዎች እውነት መናገር ቢፈልጉም እንዳይናገሩ የተለያዩ አመክንዮ ይሰጣሉ። ከፊሎችም በወያኔ አምባገነን አገዛዝ ተጠልፈው የሥርዓቱ ከዳሚና ደንገጡር በመሆን ከእውነትና ከእራሳቸው ጋር ተጣልተው የሕሊና እስረኞች ሆነው መኖር ጀምረዋል። አብዛኛው ህዝብ ደግሞ  ከእውነት ጋር ለመቆም፣ ለእውነት ለመታገል ጊዜና ወቅት በመጣባበቅ ላይ ይገኛል። ብዙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የወያኔን የውንብድና አገዛዝ ተቋቁመው ለእውነት ሲሉ ሰማዕትነትን እየተቀበሉ ይገኛሉ። እውነት ዘላለማዊ ሰላም የምታጎናጽፍ ከመሆኗም በላይ ድልን የምታቀናጅ አሸናፊ ናትና።
በዋናነት ለእውነት እንዳንታገል አዚምና እንቅፋት የሆነብን ወሮበላው የወያኔ ቡድን አምባገነናዊ አገዛዝ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ለእውነት እንዳንታገል ሆነናል። እውነትን በቃል ከመግለጽ ባሻገር በተግባር መኖር እንዳንችል ምክንያቶችን በመደርደር ከእውነት ታቅበናል። ለእውነት እንዳንታገል አዚም ከሆኑብን ምክንያቶች መካከል የተወሰኑትን ማንሳት እንችላለን።

  • ፍርሃት

ፍርሃት በአካል እና በሥነ ልቦና እንዲሁም በእለታዊ ኑሮያችን ላይ እንቅፋት ሊፈጥርብን/ሊደርስብን ይችላል ብሎ በማሰብ ከማነኛውም ድርጊት ወይም ማድረግ ካለብን ነገር መቆጠብ/መከልከል ማለት ነው። ፍርሃት ከነጻነትና ፍትህ እጦት የሚመጣ በሽታ ነው። ፍርሃት ቅጣትን ወይም ብቀላን በመፍራት ማድረግ ከምንፈልገው ሁሉ መታቀብ ማለት ነው። ፍርሃት በቡድንም ሆነ በግለሰብ ሊከሰት ይችላል፤ በሀገርና ህዝብ ላይ ግን ሊከሰት አይችልም። ፍርሃት በግለሰብና በቡድን ደረጃ ብቻም ሳይሆን በአምባገነን መንግሥታት ላይም ይከሰታል።  ስልጣንና ገንዘብ በእጅጉ ስለሚፈልጉ ይህንን ሊያሳጣ የሚችል ማንኛውንም ኃይል ይፈራሉ። ስለዚህም ህዝብን በማሰቃየት፣ በማሰርና በመግደል ስልጣናቸውን ያራዝማሉ። ግለሰቦች ይህን መከራና ስቃይ ስለሚፈሩ ለእውነት ከመታገል ወደ ኋላ ይሸሻሉ። ፍርሃት እንደ ህወሓት አምባገነን ገዥዎችን በህዝብ ላይ ስቃይና መከራን የበለጠ እንዲያጸኑ ያደርጋቸዋል፤ ብዕር ይዘው ስለ እውነት የሚታገሉትን፣ ለነጻነት ስርዓቱን የሚቃወሙ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጦማርያንን እና ወጣቱን ትውልድ በአሸባሪነት ተከሰው ግዞት እንዲወርዱ አድርጓቸዋል። የሃይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ እውነት ከመናገር ይልቅ ተቋሜ ችግር ሊገጥመው ይችላል በማለት በፍርሃት ተውጠው አምልኮታቸውን እንኳ በስርዓት ማካሄድ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ስለዚህ ፍርሃት በሁሉም በኩል ለእውነት እንዳንታገል ትልቅ እንቅፋት ሆኖብናል።

  • አድርባይነት/ጊዜያዊ ጥቅም መሻት

ለእውነት እንዳንታገል ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል አድርባይነት አንዱ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተዘግቦ እንደምናገኘው ኤሳው ለሆዱ ብሎ በምስር ወጥ ብኩርናውን አሳልፎ ለወንድሙ ለያዕቆብ እንደሸጠው ሁሉ ዛሬም በዚህ ዘመን ለጊዜያዊ ጥቅም ተብሎ ማንነትንና ሕሊናን በመሸጥ ለእውነት ከመቆም ይልቅ አድርባይነትን ተቀብለው ከእውነት ጋር የተጣሉ በርካቶች ናቸው። አድርባይነት ዛሬ የጀመረ ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አሉታዊ ተጽኖ ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል ትልቁን ስፍራ ይዞ እናገኘዋለን። በአድርባይነት ታውረው በጣሊያን ወረራ ዘመን መንገድ እየመሩ ወደ መሀል ሀገር ከማስገባት በተጨማሪም የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ባልሙዋል ከነበሩ መኩዋንንቶች እና መሳፍንቶች መካከል ሳይቀሩ ለጣሊያን ያደሩ ሰዎችን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ በአድርባይነት የተጠቁ ወገኖች ወይም ሹማምንቶች ህዝቡ ተቃውሞውን በማቆም መሰሪዋ ጣሊያን ይዛው የመጣችውን የይምሰል እውቀት እና ስልጣኔ በመቅሰም ሀገሩን ያለማ ዘንድ በሀሰት ለመሸንገል ሞክረዋል። መረጃ በመስጠት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደማቸው በግፍ እንዲፈስ ያደረጉት አድርባዮች/ጥቅመኞች ናቸው። ዛሬም አድርባኞችና ጥቅመኞች ጊዜያዊ ሥልጣንን እና የወያኔን ትርፍራፊ በመልቀም የሀሰት “ልማታዊ መንግስት” የሚል ስም ለጥፈው ሀገርን በመሸጥ፣ ታሪክን በመበረዝ፣ ህዝብን በመበደል፣ በማሰርና በመግደል ዋነኛ ተባባሪዎች እነርሱ ናቸው። ስለዚህ ከአድርባይነት ተላቀን ማንነትንና ሕሊናን በጥቅም ሳንሸጥ እንደ ዜጋ ለሀገር በማሰብ ለነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ በጽኑ መታገል ይኖርብናል።

  • ምን አገባኝነት

እኔ ከሞትኩ ሰርዶ/ግጦሽ አይብቀል እንዳለች አህያ እኔ ከበላሁ፣ ከጠጣሁ፣ ኑሮዬ ከተሟላልኝ ለሌላውና ለሚቀጥለው ትውልድ አይመለከተኝም በማለት ለነጻነት ከሚደረገው እውነተኛ ትግል የሚርቁት ጥቂቶች አይደሉም። የራሳቸው በር እስካልተንኳኳ ድረስ የሌሎች ስቃይ፣ በደል፣ ሰቆቃ፣ እንግልትና ስደት አይመለከተንም በማለት ከሰባዊነት ወጥተው ከዳር የቆሙ በርካቶች ናቸው። ምን አገባኝነት የማንነት፣ ሀገራዊና የነጻነት ጥያቄ እንዳናነሳ እና ሆድ አምላኪዎች በማድረግ ለእውነት እንዳንታገል ያደርጋል።

  • የእውቀት ማነስ

በእውቀት የበለጸገ ትውልድ ሀገርን የመለወጥ አቅም ይኖረዋል። እውቀት ሙሉ ሰው በማድረግ ሀገርን ከማነኛውም አሉታዊ ተጽኖ  በመታደግ ወርቃማ ታሪክ መስራት ይችላል። አባቶቻችን በዚህ ተክህነውበት ነበር፤ ተፈጥሯዊና በልምድ የቀሰሙትን እውቀት ለሀገር ጥቅም በማዋል በተግባር አሳይተዋል። የሀገርን ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ እንዲሁም የህዝብን ምንነት መረዳትና ጠንቅቆ ማወቅ ሀገራዊ ፍቅር እንዲኖረን ያደርጋል። የበለጸጉ ሀገራት ታሪክንና ብሄራዊ ስሜትን በማስረጽ እያንዳንዱ ትውልድ ለሀገሩ ፖሊስ (እንደ ኢትዮጵያ ፖሊስ ማለቴ አይደለም) እንዲሆን አድርገዋል። ወያኔ ግን ትውልዱ እውቀት አልባ፣ ታሪክ የለሽ ለማድረግ በጎጥና በመንደር ከፋፍሎ ሀገራዊ ስሜት እንዳይኖረው በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ይገኛል። ይህ የእውቀት ማነስ ትውልዱ ሀገራዊ ፍቅር ተላብሶ ለእውነት እንዳንታገል አድርጎናል። ወያኔዎች “በጣሊያን ቅኝ ግዛት በተገዛን ኑሮ” የሚል ትውልድ በማፍራት ሥልጣናቸውን ለማስረዘም እየጣሩ ነው። እውቀታችንን በማዳበር እንደ አባቶቻችን ታሪክ መስራት እንኳ ቢያቅተን ታሪካችንን አስጠብቀን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ሀገራዊ ኃላፊነት አለብን የሚል እምነት አለኝ።

  • ተስፋ መቁረጥ

የህግ የበላይነት ባልሰፈነበት፣ አምባገነን መንግሥት በሰለጠነበት፣ ድህነት በተንሰራፋበት ሀገር እውነት መናገርም ሆነ ለነጻነት መታገል ውጤት አይኖርም በሚል ተስፋ የቆረጠ የህብረተሰብ ክፍል በግልጽ ይታያል። ይህ ችግር በተለይ ወጣቱን ትውልድ ለእውነት ከመታገል ይልቅ ስደትን አማራጭ መፍትሄ አድርጎ እንዲጓዝ አድርጎታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዘረኝነት፣ ማን አለብኝነት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በእጅጉ ገዝፎ በመታየቱ ብዙዎችን በቀላሉ የማይቀረፍ ስለሚመስላቸው ተስፋ መቁረጥ ይታይባቸዋል። ተስፋ መቁረት መፍትሄ እንዳልሆነ ቢያውቁትም ለጊዜ ጭቆናን በጸጋ ተቀብለው ሰማያዊ ኃይል በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ብዙዎች ይመስሉኛል። ለውጥ ለማምጣት፣ ተስፍ ለመሰነቅ፣ እውነትን ለማንገስ፣ ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራስን ለማስፈን ችግሮቻችንን ተቋቁሞ ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል እንጂ ተስፋ በመቁረጥ ለስደት እና ለባርነት መጋለጥ የለብንም።
በአጭሩ ከላይ የዘረዘርናቸው ምክንያቶች/ችግር ለወሮበላውና ማፍያ ቡድን ወያኔ አሳልፎ በመስጠት ስቃይና መከራ፣ እንግልትና ሰቆቃ፣ እስራትና ግርፋት፣ ሞትና ስቅላት እንድንቀበል አድርጎናል። ብዙኃኑ ህዝብም ይበላው ይጠጣው አጥቶ፣ ነጻነቱን ተገፎ በድህነት ይሰቃያል፤ ለእውነት እንዳንታገል ትልቅ እንቅፋት ሆኖብናል። ታሪክ እንደሚያስረዳን አባቶቻችን ለእውነት ሲሉ ህይወታቸውን አሳልፈው ሰጠዋል። ዛሬም ብዙዎች መከራን እየተቀበሉ ይገኛሉ። እኛም የእነሱን ዓርያ ለመከተል እና ሀገርን ነጻ ለማውጣት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል። ለእውነትኛ ትግል እንደ መፍትሄ ሊደረጉ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

እራስን መሆን/ ለሕሊና መኖር

ማንኛውንም ተግባር ለመፈጸም ቀዳሚው ነገር እራስን መሆን ነው። እራሳችንን በሚገባ ሳናውቅና ሳንረዳ የምናከናውናቸው ነገሮች ዘላቂነት ላይኖራቸው ይችላል። በይምሰልና በሌላ አካል ተጽኖ የምንፈጽማቸው ጉዳዮችም  እንዲሁ ውጤታቸው አያምርም። ስልጣን፣ ገንዘብ፣ ጥቅም ዜያቸውን ጠብቀው ይጠፋሉ። እራስን ለመሆን ሕሊናን ማዳመጥ ይኖርብናል። ሕሊና በእድሜ ዘመናችን ሁሉ እውነተኛ ዳኛ በመሆኑ ትክክለኛ ፍርድ ይሰጣናል፤ ሕሊና ዘላለማዊ ሰላም አልያም ደግሞ ዘላለማዊ ጸጸት ያጎናጽፈናል።  እራችንን መሆን ከቻልን ለእራሳችን፣ ለእውነት፣ ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለሀገር እና ለወገን መታገል እንችላለን።  እውነተኛ ትግልን ከእራስ እንጀምር፤ ያኔ ለውጥ ማምጣ እንችላለንና።

ታሪክን በሚገባ መረዳት

ኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ፣ ባህል እና ኩሩ ህዝብ ያላት ሀገር ናት። የህዝቧ ጀግንነት፣ አይበገሪነት፣ ዳር ድንበር ጠባቂነት እና የጥቁር አፍሪካውያን ተምሳሌነት  በዓለም የተመሰከረላት ብርቅዬ ሀገር ናት። ሀገራችን የመለያየት፣ የሙስና፣ የዘረኝነት እና ተስፋ ያጣ ትውልድ መፍለቂያ አልነበረችም፤ እንደ ሀገር ዛሬም አይደለችም። ይኸን ታሪኳን ብዙ መዛግብት ይመሰክራሉና ማስተባበል አይቻልም። ቀደምት አባቶቻችን የከፈሉት ዋጋ እንዲሁ በታሪክ ሲወሳ ህያው ሆኖ ይኖራል። ታሪካችንን በሚገባ ተገንዝበን እንደ ዜጋ መክፈል የሚገባንን ዋጋ በመክፈል ለእውነት/ለሀገር መቆም አለብን። ታሪክ ሰርተን እንጂ ታሪክ በርዘን ወይም አጥፍተን ለልጆቻችን ማስተላለፍ የለብንም።

በእውቀት እራስን ማነጽ

ከላይ እንዳየነው የእውቀት ማነስ ሀገርን ወደኋላ ያስቀራል፤ ማንነትን ያሳጣል፤ ደካማና ፈሪ ያደርጋል። በእውቀት ከታነጽን ግን ለምን፣ እንዴት እና መቼ እንደምንታገል በደንብ ተረድተን ከዓላማችን እንደርሳለን። እውቀት በዓላማና በስልት እንድንታገል ይረዳናል። ነጻነት፣ፍትህ፣ ዲሞክራሲ እና ልማት ምን ማለት እንደሆነ እንረዳለን። እውቀት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለይቶ ያወጣል። እውቀት ወያኔ እንደሚያወራው ህንጻ መገንባት፣ መንገድ መስራት፣ ግድብ መገደብ፣ የሀገሪቱን ለም መሬት ለውጭ ባለሃብቶች ማቀራመት፣ ህዝብ ሃብት ንብረት አፍርቶ ከሚኖርበት ማፍለስ እና ወዘተ የዘላቂ ልማት መገለጫ እንዳልሆነ እንድንረዳ ያደርጋል። እውቀት ከምንም በላይ ለሰባዊ መብት፣ ለነጻነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ እንድንቆም እና በጽኑ እንድንታገል ከፍተኛ አስተዋጾ አለው። ስለዚህ በእውቀት መታነጽ ያስፈልጋል።

አንድነትን መፍጠር

ስለ አንድነት ብዙ መተንተን አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፤ በተግባር እንጂ በቃላት የሚገለጽ አይደለም። አባቶቻችን በተግባር አሳይተውናልና። በእውነት ወያኔን ከህዝብ ጫንቃ ላይ አሶግዶ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት ከሆነ የማስመሰል ሳይሆን እውነተኛ ህብረት/አንድነት ይኑረን። በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ተለያይተን ለውጥ ማምጣት በፍጹ የማይታሰብ ነው። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው ተባብረን በአንድ ላይ ከቆምን እንኳን ወያኔን ጣሊያንን ድባቅ የመቱ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ልጆች ነንና ጊዜ ሳይፈጅብን ሀገራችንን ነጻ ማውጣት እንችላለን።  ስለዚህ አንድነት ይኑረንና ከዘረኛው ወያኔ እራሳችንና ሀገራችንን ነጻ እናውጣ!

በአጠቃላይ ለእውነት እንዳንታገል አዚም የሆነብንን ነገር አሶግደን ከእኛ የሚጠበቀውንና ጊዜው የሚጠይቀውን ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል ለእውነት ከቆሙ እና ከነጻነትና ፍትህ ታጋዮች ጋር በመቀላቀል በይፋ እውነትን መስበክ ሀገራዊ ግዴታ አድርገን እንነሳ። እኛ በውጭም በውስጥም የምንኖር ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያን የወያኔ ተራ የሃሰት ወሬና ማስፈራሪያ ሳይገድበን ለነጻነትና ፍትህ በጽናት እንታገል። ለእውነት፣ ለሀገር፣ ለነጻነትና ፍትህ ብለው ስቃይና መከራ፣ እስራትና ግርፋት እንዲሁም ሞት የተፈረደባቸውን እውነተኛ ታጋዮችን በማሰብ  የእነርሱን ራዕይ እና ሀገራዊ ተልእኮ ከግብ ለማድረስ እኛ ለእውነትና ለእውነት ብቻ በመታገል ሀገርራችንን ከወያኔ ዘረኛና አምባገንን አገዛዝ እንታደግ።

 

ለእውነትና ለእውነት ብቻ እንታገል! አዚም የሆነብንን ወያኔን በነገር ሁሉ እንቃወም!!!

ምንጭ:

http://yibeltalethiopia.blogspot.no/2015/06/blog-post.html