0
Posted February 8, 2013 in Amharic news
 
 

የወያኔ ጀሃዳዊ ሀረካት ድራማ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ እንደማያዳፍነው ተገለጸ


ህዝብን ርስ በርስ በማጋጨትና በማዋጋት ራሱን በስልጣን ኮርቻ ኮፍሶ ለዘመናት መጉዋዝ የሚፈልገው ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ ከትናንት በስቲያ በቁጥጥሩ ስር አድርጎ እንደፈለገው በሚጫወትባቸው ሚዲያዎቹ ያስተላለፈው ጀሃዳዊ ሃረካት ድራማ በኢትዮፕያዊያን እየተጣጣለና እየተወገዘ መሆኑን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ አመለከተ።

እንደዘጋቢያችን ሪፖርት በሃገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል እየተንቀሳቀሰ ያለው አንድነት ፓርቲ  ” በ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› ትረካ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም!” በሚል ርእስ  መግለጫ፣  ማውጣቱ ታውቁአል። አንድነት በዚሁ መግለጫው በገዢው ፓርቲ ድርጊት ማፈሩንና ማዘኑን ገልጾ የከትናንት በስቲያ አዲስ ድራማው  ገዥው ፓርቲ  ዜጎች በማንኛውም መንገድ የሚያነሱትን ጥያቄ በግልጽና በውይይት መፍታት ያለመፈለጉ ግልጽ ሀገራዊ አደጋ እየሆነ መምጣቱ እየታየው ነው  ብሉአል። በመቀጠልም  ”ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሀገር እያስተዳደረ ባለ አገዛዝ” ማዘኑን ገልጾ  በኢትዮጵያ ሕዝብ ግብር የሚተዳደረው ነገር ግን የገዥው ፓርቲ መሳሪያ በመሆን የሕዝብ  ጥያቄዎችን ለማፈን ተባባሪ መሳሪያ ሆኖ እያለገለ ያለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› በሚል የተሰናዳና እንደተለመደው የሙስሊሙን ህዝብ ጥያቄን ለማዳፈን የተዘጋጀ አይነት ትረካ ሲያቀርብ የመጀመሪያው አለመሆኑን አስታውሷል።

በበረከት ስምኦንና በጓደኞቹ ተቀነባብሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሊቀርብ ሲል በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የታገደዉ “ጂሀዳዊ ሀረካት” የሚባል ፊልም እገዳዉ በተሰማ በሰአታት ውስጥ በወያኔ ባለስልጣኖች ግፊት ተነስቶ ፊልሙ በኢቲቪ የታየ መሆኑን በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።

ኢቲቪ ያቀረበው ፊልም የኢትዮጵያን እስልምና እምነት መሪዎች ከአልሸባብና ከአልቃይዳ ጋር በአንድ ጎራ መድቦ የሚወነጅል ሲሆን በብዙዎች ግምት የፊልሙ ዋና አላማ ከአንድ ሺ አመት በላይ በሰላም ተከባብረዉ የኖሩትን ሁለቱን ትልልቅ የኢትዮጵያ  ሀይማኖቶች  እርስ በርስ እንዲጋጩ ለማድረግ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት ይህ የሙስሊሙንና የክርስቲያኑን ህብረተሰብ ለማጋጨት ሆን ተብሎ ከመንግስት ካዝና በወጣ ገንዘብ የተሰራ ፊልም ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የስልጣን ዘመኔን ያራዝምልኛል ብሎ ካመነ ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ በግልፅ ያሳያል ብለዋል።

ባለፉት ሃያ አንድ አመታት ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ጠንክሮ የተቃወማቸዉንና ህዝብ የሚወዳቸዉን ድርጅቶችና ግለሰቦች “ህገመንግስት አፍራሽ” ወይም  “ሽብርተኛ” የሚል ስም በመለጠፍ  ፊልምና ድራማ  እየሰሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማታለል መሞከራቸዉ የሚታወስ ነዉ። ህዝብ በሠላማዊ መንገድ የሚያቀርብለትን ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ ህዝብን መደፍጠጥ የሚቀናዉ ወያኔ ከሰሞኑ “ጂሀዳዊ ሀረካት” የሚባል ፊልም አቀነባብሮ ለህዝብ ያቀረበዉ ላለፉት 12 ወራት ሽንጣቸዉን ገትረዉ የታገሉትን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለማሰር፤ለመደብደብና ለመግደል የሚያስችል ይሁንታ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከአለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚያስገኝለት መስሎት ነዉ።

የፊልሙን ይዘትና ቅርጽ አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን በስልክ ያናገራቸዉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የወያኔ አገዛዝ ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን በማጣላት በአንድ በኩል የክርስቲያኑን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሙከራ እያደረገ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሁለቱን የሐይማኖት ህብረተሰቦች በማጣላት ህዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ በሚያደርገዉን ትግል ላይ ዉኃ ለማፍሰስ የሚያርገዉ ከንቱ ሙከራ እንደሆነ ገልጸዋል። አንድ ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁን የእስልምና እምነት ተከታይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋና አዋቂ በመሆኑ በወያኔ  ፕሮፓጋንዳ ተታልሎ  እርስ በርሱ አይጋጭም ካሉ በኋላ ይህንን ርካሽ የወያኔ ፕሮፓጋንዳና የዉሸት ማስጠንቀቂያ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አይሰማዉም ክርስቲያኑም ቢሆን በጭራሽ አይቀበለዉም ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢቲቪ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም”ይድረስ ለሁሉም” የሚልና በኢቲቪ የተላላፈዉን የወያኔ ድራማ የሚኮንኑ  የኤስ ኤም ኤስ መልእክቶች  በመላ አገሪቱ ተሰራጭተዋል።

ለየት ባለ ዜና ደግሞ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ከተሰራዉ ድራማ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉና ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስን፤ ብጹዕ አቡነ መልክአ ጻዲቅንና ብፁዕ አቡነ መቃሪዎስን በሽብርተኝነት የሚፈርጅ  ዶክመንተሪ ፊልም ተጠናቅቆ በቅርብ ግዜ ውስጥ ለህዝብ ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።  ፊልሙ አቡነ መርቆሪዎስን ነፍጥ ካነሱ ሀይሎች በተለይም ከግንቦት ሰባትና ከከአርበኞች ግንባር ጋር ይሰራሉ በሚል የፈጠራ ወንጀል  ይወነጅላል። በዚህ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርባል ተብሎ በሚጠበቀዉ ድራማ ላይ ወያኔ አጋሮቹ የሆኑትን የሐይማኖት አባቶች በአስረጂነት የሚያቀርብ ሲሆን በዚህ የሀሰት ድራማ ላይ አንሳትፍም ያሉ አባቶች ካሁኑ የወያኔ ጫና መዉጪና መግቢያ እያሳጣቸዉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።