0
Posted January 18, 2013 in Amharic news
 
 

ፍሬ አልባ በለሶች!!!


አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የጥበብ ሰዎችን አፍርታለች። ሀዲስ ዓለመየሁን፤ በዓሉ ግርማን፤ ብርሃኑ ዘሪሁንን፤ አቤ ጉበኛውን፤ ሎሬት ፀጋየ ገ/መድህንን፤ ጥላሁን ገሰሰን አንረሳቸውም። እነዚህ የጥበብ ሰዎች የህዝባቸውን ልቅሶ ያለቀሱ፤ ሃዘኑን ያዘኑ፤ብሶቱን ከፍ ባለ ድምጽ የተናገሩለት እና እውነትን የፈለጉ ስመ ጥር ባለሙያዎች ነበሩ። እነዚህ ባለሙያዎች እንደ እሥሥት ራሳቸውን ሳይቀያይሩ ለሂሊናቸው ታምነው፤ በጥበባቸው ስለ እውነት ሰብከው ያለፉ ስም ጥር ባለሙያዎች በመሆናቸው ተረስተው የሚቀሩ አይደሉም።

ዛሬም የእነዚህን ስም ጥር ባለሙያዎችን መስመር የሚከተሉ አሉ። ህዝብ ሲያለቅስ አብረው የሚያለቅሱ፤ የህዝቡን ብሶት የሚናገሩለት፤ ከሂሊናቸውና ከእውነት ጋር መቆምን የመረጡ ብርቅየ የጥበብ ሰዎች አሉ። ሥራቸው በሮሮ ውስጥ ላለ ህዝብ ተስፋ፤ አቅም የለኝም ለሚለው ብርታት የሚሆን እንደ ቤተ መቅደስ እጣን መዓዛው ያመረና የተወደደ ነው። እነዚህ የጥበብ ሰዎች የህፃን ነብዩን እንባ አይተው ዝም ማለትን ያልመረጡ፤ ሰው በዘሩ ብቻ ተመርጦ ሲዋረድ፤ በዘሩ ብቻ ተመርጦ ሲሾም እያዩ ምን አገባኝ ያላሉ፤ አገሪቷን አገር ሊያሰኙ የሚችሉ ወግና ልማዶችን ከሚያጠፉ ቡድኖች ጎን መቆምን የተጠየፉ፤ ጥቂቶቹ ብዙሃኑን ተጭነው፤ ብዙሃኑም ጥቂቶቹን ተሸክመው ስቃያቸው በዝቶ ሲኖሩ አይተው እንዳላዩ መሆንን እንደ ውረደት የቆጠሩ፤ ብኩርናቸውን ለምናምንቴ ነገር ሲሉ አሳልፈው ያልሰጡ ብርቅየ ልጆች አሁንም ኢትዮጵያ አሏትና ደስ ይለናል።

የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ሆነና ብኩርናቸውን በምናምንቴ ነገር ለውጠው ከህብረተሰቡ ተነጥለው ብቻቸውን በበርሃ የቆመን ፍሬ አልባ በለስ የሚመስሉ ደግሞ አሉ። እነዚህ ራሳቸውን ከጥበብ ሰዎች ተርታ ለማቆም ቢውተረተሩም እንደ ፍሬ አልባዋ በለስ ባዶ በመሆናቸው ለትውልዱ የሚተውለት መልካም አሻራ ከእነዚህ ዘንድ አልተገኘም። ግዜ ካነሳው ጋር እየተነሱ፤ ግዜ የጣለውን ደግሞ እየረገጡ ራሳቸውን እንደ እሥሥት እየቀያየሩ የሚገለጡ አርቲስት ተብየዎች በነሎሬት ፀጋየ ገ/መድህን፤ በነበዓሉ ግርማ፤ በእነ አዲስ ዓለማየሁ፤ በእነ ብርሃኑ ዘሪሁን፤ በእነ አቤ ጉበኛ አገር መፈጠራችው በእጅጉ ይገርማል።

ጥበብ እውነት ነች። የጥበብ ሰው መሆን ማለትም የእውነት ሰው ማለት ነው።የጥበብ ሰው ከሌላው ተራ ህዝብ የተለየ ነው። የጥበብ ሰው ክብሩና ሞገሱ ለእውነት መቆምና እውነትን መፈለግ እንጂ እንድ ዔሳው ብኩርናውን ዛሬ ተብልቶ ነገ ለሚረሳ ምስር ወጥ የሚቀይር ማለት አይደለም። የጥበብ ሰው ህይወቱ እውነትን መፈለግ እና ለእውነት ዘብ መቆም ነው። ያ እርሱ ፈልጎ የገኘውን እውነት፤ ያ እርሱ ዘብ የሚቆምለትን እውነት በልዩ ተሰጥኦው ለህዝቡ ማስተማርና የአሰተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ መጣር ደግሞ መጨረሻው የህይወት ግቡ ነው። እውነትን ያልፈለገ እና እውነትን በህረተሰቡ ውስጥ ማስረፅ የተሳነው የጥበብ ሰው እንደ ሌለ ራሱን ቢቆጥር ይሻለዋል። የጥበብ ሰው የህብረተሰቡ ፋና ወጊና አስተማሪ ነው ተብሎ ሊወደድ የሚችለው ለእውነት ዘብ ለመቆም ወኔው ያለው በመሆኑ ነው። ለእውነት ዘብ መቆምን የመረጠ ግዜ በህብረተሰቡ ፊት ሞገስና ክብርን ያገኛል፤ ሲያልፍም ስሙ በደጉ እየተነሳ ይኖራል እንጂ ተረስቶ አይቀርም።

ከዥንጉርጉሩ የእናት ሆድ የተወለዱ ሌሎች “የጥበብ ሰው” ነን የሚሉ ብዙ ናቸው።ከጥበብ ጋር ግን ራሳቸውን ለማዋሃድ ወኔውን ማጣችውን ባየን ግዜ  በእጅጉ እናፍራላቸዋለን። እነዚህ በኢቲቪ መስኮት ብቅ ብለው በህፃን ነብዩ ደምና አጥንት ላይ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮና ረዝሞ የተሠራውን ህንፃ ብቻ ተመልክተው፤ ያን ህያው ብላቴና ረስተው ግዑዙን ህንፃ ብቻ የሚያደንቁትን አርቲስት ተብየዎችን ማየት በእውነት አሳፋሪ ነው። የጥበብ ሰው ከግዑዝ ይልቅ ህይወት ላለው ህያው ነገር ይራራል፤ህመሙ  ያመዋል፤ ራቡ ይርበዋል፤ ስቃዩ ያሰቃየዋል እንጂ የድንጋይ ቤት ርዝመት አያስደምመውም። ከጥበብ ጋር ያልተዋሃደ እና ብኩርናውን ለምናምንቴ ነገር አሳልፎ የሰጠ ግን እንዲህ ነው። ከህያው ነገር ይልቅ ህይወት የሌለው የማይናገር፤ የማይስቅ፤ የማይሰማ ግዑዝ ነገር ልቆ ይታየዋል።

ከሰሞኑ ደግሞ አርቲስቶች የተባሉት ተሳብሰበው የህወሃትን ጦር ሰፈር ጎበኘን ማለታቸውን ሰምተናል። ይሄ ምንም ችግር ያለው ነገር አይደለም። የጎበኙት የጦር ሰፈር ግን ለኢትዮጵያ ክብርና አንድነት የሚሰራ ሳይሆን አገሪቷን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ እንዲያውም “አማራና ተፈጥሮ የትግራይ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው” ብሎ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጠላትነትን ለመተክል ሌተ ተቀን በሚሰሩ ቡድኖች የሚመራ መሆኑን ለማስታወስ ግዜው አሁን ነው። ይሄን የጦር ሰፈር የሚመሩት በአንዲት ጀንምበር በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ ንፁሃን ዜጎችን የገደሉ ናቸው። ይሄን የጦር ሰፈር የሚመሩ ቡድኖች በጋምቤላ እና በዖጋዴን ህዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀሙ ናቸው። ይሄን የጦር ሰፈር የሚመሩ ሰዎች የዜጎችን የእምነት ነፃነት በመጋፋት እኛ የመርጥነውን አምላክ አምልክ እምቢ ካልክ ግን አሸባሪ ነህ ብለው ንጹሃን ዜጎችን የሚያሸብሩ ቡድኖች ናቸው። ይሄን የጦር ሰፈር የሚመሩት ቡድኖች እጅግ ኋላ ቀር ዘረኞች፤ ከመንደራቸው ዘልቀው ሂደው ማሰብ የማይችሉ መንደረተኞች ናቸው። ይሄን የጦር ሠፈር የሚመሩ ቡድኖች ህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ እንዳይኖረው መገናኛ ብዙሃንን አፍነው፤ ጋዜጠኞችን አስረው፤ ገድለው፤ ከአገር አሳደው፤ ዜጎች በነፃነት እንዳይፅፉ፤ በነፃነት እንዳያስቡ፤ በነፃነት እንዳይናገሩ ያደርጉ ናቸው።

በእነዚህ ቡድኖች ለጉብኝት የተጋበዙ አርቲስቶች ብረቱን ብቻ ሳይሆን ከብረቱ ጀርባ ያለውንም እውነት ለማየት የሚያስችል ማስተዋል አይኖራቸውም ብለን ተስፋ አንቆርጥም። ዛሬ ህወሃቶች ገንብተነዋል የሚሉትን ብረት ለምንና እንዴት ሲጠቀሙት እንደቆዩም ዞር ብለው መርምረው እውነቱን ለማግኘት ብቃቱ አላቸው ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እነዚያ ብረቶች ከተማሪ ቤት ሲመለስ የነበረውን ነብዩን ደብደበው የገደሉ መሆናቸውን እንደሚያስታውሱም እናምናለን። ነብዩ ከመሞቱ በፊት ያን ጨካኝ የህወሃት ነፍሰ ገዳይ እባክህ አትግደለኝ እያለ ሲማፀን፤ ሲያለቅስ ሲያነባ በዓይነ ሂሊናቸው ማየት ይችላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እነዚያ ብረቶች የንፁሃንን ደም በከንቱ አፍሠሰዋል። እነዚያ ብረቶች በጋምቤላ፤ በዖጋዴን፤ በአማራ፤ በኦሮሚያ ያፋሰሷቸው ደሞች እንደ አቤል ደም ከምድር ወደ ሰማይ እየጮኹ ነው።ያንን ጩኸት ለመስማት ደግሞ እንደ በረከት ስምዖን ራሳቸውን ይክዳሉ የሚል እምነት የለንም።

አሁን በኢትዮጵያችን ውስጥ ያለው እውነት ይሄው ነው። አርቲስቶቹ የጥበብ ሰው ነን ካሉ፤ ህዝቡ ፊት ለመቆም የሞራል ብቃት አለን ካሉ ከዚህ እውነት ጋር መጋፈጥ ይጠበቅባቸዋል። ስራቸው እንደ መልካም መዓዛ በህዝቡ ዘንድ እንዲወደድ ከፈለጉ በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ኢፍታህዊነት፤ ዘረኝነት፤ አድልዎ፤ ጭቆና፤ እንዲሁም የህዝቡን ሮሮ ወደ አደባባይ ማውጣት ይኖርባቸዋል። እውነቱን እምቢ ብለው ከጨካኞቹና ከዘረኞቹ ህውሃቶች ጋር መቆምን ከመረጡ ግን ምርጫቸው ሁል ግዜ እንዳሳፈራቸው ይኖራል እንጂ የሚያስከብራቸው አይሆንም።

በመጨረሻም እናንተ አርቲስቶእች አድምጡን ገንዘባችሁ ህዝብ እንጂ ህወሃት አይደለም። ብትዘፍኑ የሚያዳምጣችሁ፤ ብትቀልዱ የሚስቅላችሁ፤ ብትጽፉ የሚያነብላችሁ ህዝብ እንጂ ዘረኛው ህወሃት አይደለም። ህወሃት የህዝብ ጠላት መሆንን የመረጠ የወሮበላዎች ስብሰብ ነው። ከህወሃት ጎን መቆም በክፉዎች መንገድ መሄድን መምረጥ ነውና አያስመሰግንም።ኢትዮጵያችን ውስጥ በዘረኞቹ ህወሃቶች የሚፈፀመውን ወንጀል ደግፋችሁ ከእነርሱ ጎን መቆምን ከመረጣችሁ ግን ፊሬ አልባዋን በለስ መሆንን መርጣችኋልና ያሳፍራል።

እዚህ ላይም ጥላሁን ገሰሰ “ሃብቴ ህዝቤ፤ ሃብቴ አገሬ” ያለውን አስታውሱ። በእኛ በኩል አበቃን።

ድል ፍትህንና እውነትን ለሚፈልጉ ሁሉ ይሁን !!!